የተለያዩ ነጋዴዎች ምሬታቸውን ገለጹ

መጋቢት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስአበባ እና በክልል ዋና ዋና ጅምላ ማከፋፈያ ቦታዎች የሚካሄደው ሽያጭ ማዕከላዊ የግብይት ስርዓት ያልጠበቀ አሰራር በመሆኑ በገንዘብ ደረሰኝ መመዝገቢያ ማሽን (ካስሪጂስተር) ለመስራት ትልቅ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡
በኢህአዴግ ንብረትነት በሚተዳደረው የአምባሰል ንግድ ስራዎች ድርጅት በብቸኝነት በሚቀርበው የገንዘብ ደረሰኝ መመዝገቢያ ማሽን (ካሽሪጂስተር) ለመስራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በአማራ ክልል የሚገኙ ነጋዴዎች ለኢሳት ተናግረዋል፡፡
በሃገሪቱ ያለው የንግድ አሰራር ስርዓት ወጥ ባለመሆኑ በደረሰኝ አሰጣጥ ዙሪያ ችግር እንደፈጠረባቸው የሚናገሩት ነጋዴዎች ፤በአዲስ አበባ በአስመጭና አከፋፋይነት በስፋት እየሰሩ ባሉት የስርዓቱ ሰዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር የላላ በመሆኑ በደረሰኝ ለመግዛት ከፍተኛ ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አብዛኛው ዕቃ ያለደረሰኝ ለሚገዙ ነጋዴዎች እንደሚመቻች የሚናገሩት ተጨማሪ እሴት ከፋይ ነጋዴዎች ደረሰኝ እንዲጻፍላቸው ሲፈልጉም ዋጋውን በግማሽ በመቀነስ ስለሚጽፉባቸው የገንዘብ ደረሰኝ መመዝገቢያ ማሽን ተጠቅመው ለመስራት ችግር እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡
“ያለደረሰኝ በመግዛት ያለደረሰኝ የሚሸጡ የደረጃ ሐ ነጋዴዎች ስላሉ ታላላቆቹ አከፋፋዮች ሸቀጣቸውን ለእነርሱ መሸጥ እንጅ ለእኛ መሸጥ አይፈልጉም፡፡” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢ ነጋዴ ፣ አብዛኛውን ጊዜ ደረሰኝ ለሚጠይቁ ሰዎች እቃው እያለ “የለም !” በማለት እንደሚመልሷቸው ይናገራሉ፡፡
“የገዥው መንግስት በየወረዳው ያለውን ነጋዴ ለማስመረርና ከስራ ውጭ ለማድረግ ባልተስተካከለ የንግድ ግብይት ስርኣት የገንዘብ ደረሰኝ መመዝገቢያ ማሽን እንድንጠቀም ያስገድደናል፡፡” በማለት የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ “በዋናዋና ከተሞች የሚካሄደውን ዓይን ያወጣ ዝርፊያና ያለደረሰኝ ሽያጭ ግን ሆን ብሎ ችላ በማለቱ ስራችንን ለማቆም እየተገደድን ነው፡፡” በማለት በምሬት ይናገራሉ፡፡