ኢሳት (መጋቢት 5 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች በኦሮሚያ ክልል በወሰዱት የሃይል እርምጃ የአገድዶ መድፈር ድርጊትን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብትን ጥሰቶችን መፈጸማቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሰኞ ይፋ አደረገ።
መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ድብደባን ጨምሮ የጅምላ እስራትና ስቃዮች ስለመፈጸማቸው ማስረጃዎች መገኘታቸውን እንደገልፀ አሶሼይትድ ፕሬስ (Associated Press) ዘግቧል።
በክልሉ ስለተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ የጸጥታ ሃይሎች የአስገድዶ መድፈርና ሆን ብሎ ሰዎችን የመግደል ድርጊቶችን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን አመልክቷል።
የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን መነሻ አድሮጎ ሌሎች የመብት ጥያቄዎችን ጨምሮ በክልሉ ተቀስቅሶ በነበረው እና አራተኛ ወሩን በዘለለው በዚሁ ተቃውሞ 103 ሰዎች መገደላቸውንም አሶሼይትድ ፕሬስ የምክር ቤቱን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ አስነብቧል። ሌሎች ረፖርቶች ሟቾቹ ከ300 በላይ እንደሆኑ አስታውቋል።
የፓርቲ አመራሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከተቃውሞ ጋር በተገናኘ ወደ አምስት ሺ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
የመንግስት ባለስልጣናት የማስተር ፕላን እቅዱ ተግባራዊ እንዳይደረግ በተደጋጋሚ ቢገልጽም ተቃውሞው አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በክልሉ በወሰዱት እርምጃ የገቡበት ያልታወቀ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ አክሎ ገልጿል።
የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ በክልሉ ግድያን የፈጸሙ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ጥያቄን ማቅረባቸውም የሚታወስ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በኦሮሚያ የቀጠለው ተቃውሞ በሳምንቱ መገባደጃ በምስራቅ ሃረርጌ በሚገኙ አካባቢዎች መቀጠሉ ታውቋል።
አወዳይን ጨምሮ በዳዳር እና አጎራባች መንደሮች በክልሉ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችን የሚያወግዙ ተቃውሞዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞን ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃም በርካታ ነዋሪዎች በጥይት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ቁጥራቸው ሊታወቅ ያልቻለ ሰዎችም ለእስር መዳረጋቸውን ለመረዳት ተችሏል።
በክልሉ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ በርካታ ሃገራትና አለም አቀፍ ድርጅቶች ስራተኞቻቸውን ወደክልሉ እንዳይጓዙ ማሳሰባቸው ይታወሳል።