ኢሳት (መጋቢት 5 ፥ 2008)
ሰሞኑን በደቡብ ክልል ኮንሶ ከአስተዳደራዊ ጥያቄ ጋር በተገናኘ የተቀሰቀሰው ግጭት ኣሁድ በድጋሚ አገርሽቶ ሶስት ነዋሪዎች መገደላቸውን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪ የኮንሶ ወረዳ ወደ ዞን ደረጃ እንዲዋቀር ጥያቄን ለክልሉና ለፌዴራል መንግስት ቢያቀርቡም ጥያቄያቸው የሃይል ምላሽን እያገኘ እንደሆነ ነዋሪዎቹ አስረድተዋል።
አካባቢው በጸጥታ ሃይሎች ተከቦ እንደሚገኝ የተናገሩት እማኞች የጸጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ጥያቄን ለማቅረብ በተሰባሰቡ ነዋሪዎች ላይ የተኩስ እርምጃን በመክፈት ሁለት ሰዎች ላይ ግድያን እንደፈጸሙ አስታውቀዋል።
የሁለቱ ሟቾችን ስም በመጥቀስ ሁኔታውን ለኢሳት ያስረዱት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ግድያ ከተፈጸመባቸው ሁለቱ ግለሰቦች በተጨማሪም በርካታ ነዋሪዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።
የክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ነዋሪዎች ያቀረቡትን ጥያቄ የእኛ አይደለም በማለት እንዲያስተባብሉ ግፊት እያደረጉ እንደሚገኝ ሲሆን፣ የኮንሶ ከተማና አካባቢዋ አለመረጋጋት ሰፍኖበት እንደሚገኝ አክለው አስረድተዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት በቅርቡ በኮንሶ የተነሳው ጥያቄ ህጋዊ ምላሽን አግኝቷል ሲሉ ምላሽን መስጠታቸው ይታወሳል።