ኢሳት (መጋቢት 5 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ በከፋ የምግብ እጥረት የሚጎዱ ሰዎች ቁጥር በአለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው 15 በመቶ በላይ መድረሱ እንዳሳሰበው የአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ይፋ አደረገ።
እየተባባሰ የመጣውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ ለከፋ የምግብ ጉዳት የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ከ20 በመቶ በላይ መድረሱን የተቋሙ ሃላፊዎች መግለጻቸውን USA Today ጋዜጣ ዘግቧል።
ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት በአለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው መጠን በላይ መሆኑንም ለእርዳታ ተቋማት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የአለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባል ቻሊስ ምክዶኑግ አስረድተዋል።
የተባባሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት በበኩሉ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት በከፋ የምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸው በመሆኑ ልዩ እንክብካቤን የሚፈልጉ እንደሆነ ገልጿል።
በርካታ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ ወደረሃብ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ በመግለጽ ላይ ሲሆኑ ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳትም ከተጠበቀው በላይ መሆኑን USA Today ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።
በኢትዮጵያ የቻይልድ ፈንድ ተወካይ የሆኑት አቶ ኢዩኤል ለማ ድርቁን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ቢቀጥልም ችግሩ ግን እየተባባሰ በመሄድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሃገሪቱ ያለን የምግብ ክምችት በቀጣዩ ወር ሊያልስ ስለሚችል የነፍስ ማዳን ስራ አስቸጋሪ እየሆነ እንደሚመጣ በድጋሚ አሳስቧል።
በድርቁ በተጎዱ አካባቢዎች ያለውን የውሃ እጥረትም ተጨማሪ ችግር እየሆነ መምጣቱን ያስታወቀው ድርጅቱ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለከፋ የውሃ እጥረት መጋለጣቸውን አክሎ ገልጿል።
ነዋሪነቷ በፈንታሌ ከተማ የሆነውና የሁለት ህጻናት እናት የሆነችው ገነት ታምራት ልጆቿ በምግብ እጥረት የተነሳ ክፉኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውና በቤታቸው ምንም ምግብ አለመኖሩን ለጋዜጣው አስረድታለች።
ተመሳሳይ ችግሮች በበርካታ አካባቢዎች መኖራቸውን የዘገበው ጋዜጣ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት የሚፈለገውን እርዳታ ለማግኘት ርብርብ ውስጥ መሆናቸውን አክሎ አመልክቷል።