ኢሳት (መጋቢት 5 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ ከውጭ በሚገቡ ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ግሽበቱ እያደገ መምጣቱን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ባለፈው ወር ተመዝግቦ የነበረው ይኸው የዋጋ ግሽበት ከ7.9 በመቶ ወደ 8.2 በመቶ ማደጉን ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው ሃገሪቱ አጋጥሟት ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በሸቀጣሸቀቶች ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ባለፈው ወር የሃገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 8.7 በመቶ የተመዘገበ ሲሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ በሸቀጣሸቀጦች ገቢ ንግድ ላይም እጥረት ማስከተሉን ተጠቃሚዎች አስታውቀዋል።
በውጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች በበኩላቸው የብሄራዊ ባንክ ተግባራዊ ያደረገው የቁጥጥር ስርዓት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ሊቀርፈው እንዳልቻለ መግለጻቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የአለም ባንክን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት አጋጥሞት ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች መውሰድ እንዳለበት በተደጋጋሚ ማሳሰባቸው ይታወሳል።