ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል በሳሊኒ ኩባንያ ላይ አቤቱታ አሰማ

መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ለአነሳ ህዝቦች መብት መከበር የሚታገለው ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል ፣ ሳሊኒ በኦሞ ወንዝ ላይ በሚያካሂደው ግንባታ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በርሃብ እንዲጠቁ ማድረጉን በመጥቀስ፣ አቤቱታውን በኢኮኖሚ የበለጸጉት አገሮች ትብብር ድርጅት (OECD) አቅርቧል።
የጣሊያን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ በኢትዮጵያና በኬንያ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮችን ህይወት ማበላሸቱን የገለጸው ድርጅቱ፣ ግንባታው የቱርካና ሃይቅን ፍጻሜ ሊያስከትል ይችላል ብሎአል።
ሳሊኒ ግንባታውን ሲጀምር የአካባቢውን ህዝብ አለማማከሩን፣ አስፈላጊውን ካሳ አለመክፈሉንና በአሁኑ ሰአት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩትን ለርሃብ መዳረጉን ድርጅቱ ገልጿል።
በቅርቡ የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል አባላት የሱርማ ተወላጆችን አንገታቸውን አስረው ሲያሰቃዩዋቸው የሚያሳየው ፎቶ በማህበራዊ ሚዲያ ከተለቀቀ በሁዋላ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስነሳቱ ይታወቃል።