ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2008)
በየዕለቱ ወደ ኬንያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያን ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የኬንያ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት መንግስት ተጨማሪ በጀትን በመመደብ የድንበር ቁጥጥሩ እንዲጠናከር ጠየቁ።
በከዋሌ አውራጃ የሚገኘው የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን ጽ/ቤት ወደ ኬንያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መጨመር ለጸጥታ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ለመንግስት እንዳስታወቀ ዴይሌ ነሽን ጋዜጣ ዘግቧል።
የግዛቲቱ የኢሚግሬሽን ኦፊሰር የሆኑት ቻርለስ ኡር ባለፉት ሁለት ወራቶች ብቻ ከ60 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በህገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ በመግባታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
በየዕለቱ የሚደረጉ ስደቶች እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ሃላፊው የሃገሪቱ መንግስት ተጨማሪ የቁጥጥር ተሽከርካሪዎች እንዲመደቡ በማድረግ የድንበር ቁጥጥሩ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
በድንበር በኩል ከሚደረገው ስደት በተጨማሪ የታጠቁ ሃይሎች በየጊዜው ድንበርን በመዝለቅ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ታጣቂዎችን ለመያዝ በሚል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከኬንያ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ስጋት መሆኑም ታውቋል።
የአለም አቀፍ ስደተኞች ተቋም በየዕለቱ በአማካይ 30 ኢትዮጵያውያን ወደጎረቤት ኬንያ በመሰደድ ላይ መሆናቸውን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ከኢትዮጵያ በመሰደድ ላይ ያሉት ስደተኞች መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ፣ ሊቢያ፣ የመንና አውሮፓ እንደሆነም ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል።
በተያዘው ሳምንት የኬንያ የጸጥታ ሃይሎች 23 ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ያዋሉ ሲሆን በፈረንጆቹ አዲስ አመት መግቢያ ላይም ከ80 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበርም የኬንያ ፖሊስ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት ጎረቤት ኬንያን ጨምሮ በሱዳን፣ የመን፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ናሚቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው በእስር ቤት እንደሚገኙም ለመረዳት ተችሏል።