መጋቢት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት ጉባዔ የቅማንትን ህብረተሰብ ወክለው የተገኙት ግለሰብ ለረዢም ዓመታት የኖሩትን ህዝቦች ለማጋጨት ሙከራ ሲደረግ ፈጥኖ ለምን እርምጃ እንዳልወሰደ አልገባኝም ብለዋል።
ተቻችለው የሚኖሩት ሁለቱ ህዝቦች በጋብቻ ተሳስረው ፣አንድ ዓይነት ባህልና ወግ ያላቸው፣ አንድ አንሶላ ተጋፈው ለብሰው የኖሩ ሆነው እያለ፣ ቅማንትና አማራ በሚል የማተራመሱን ሴራ ሲፋፍሙ በነበሩ ሰዎች ላይ ፈጥኖ በወቅቱ እርምጃ ባለመውሰዱ ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን ለምክር ቤቱ አርበዋል፡፡
“በሁለቱ ህዝቦች የተነሳ ጥያቄው የማንነት እና የራስ አስተዳደር ጥያቄ አይደለም፡፡” የሚሉት ተወካዩ “አካባቢው የልማት ቦታ እና የልማት ምንጭ በመሆኑ ሆን ብሎ ገቢውን ለማድረቅ በማሰብ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተሰራብን በደል ነው፡፡” በማለት ያለውን የህዝብ ቅሬታ በድፍረት ሲያቀርቡ ተሰምተዋል፡፡
ህብረተሰቡ ጉዳዩ ወደ ግጭት ከማምራቱ በፊት ማብረድ እንዲቻል ለገዢው መንግስት በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም፣ ሆን ተብሎ ችላ በመባሉና “ታሳየናለህ” እየተባለ ወጣቱ በመቀስቀሱ ይህ እልቂት መከሰቱን ቅሬታ አቅራቢው ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የተፈጠረው ችግር በአስቸኳይ እንዲፈታ የጠየቁት የህዝብ ተወካይ አሁንም ቢሆን ይህ ግጭት እንዲፋፋም የሚያደርጉት ግለሰቦች በይፋ እየታወቁ ገዢው መንግስት በዝምታ የሚመለከትበት ሁኔታ ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ግጭቱ እንደገና ከተቀሰቀሰ እስከ መጨረሻው የማይበርድበት ደረጃ የሚደርስ መሆኑን አሁንም ሙሉ በሙሉ በርዷል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል።
“በሱዳን ድንበር በኩል ያለውን ስጋትም መንግስት ችላ ብሏል፡፡” በማለት የሚወቅሱት ተወካዩ፣ አካባቢው የልማት ቦታ ቢሆንም የሱዳን ሰዎች ወደ አማራ ክልል በመግባት ዝርፊያ ሲያካሒዱና የክልሉ ሰዎችም ወደ ሱዳን በመዝለቅ አጸፋውን ሲመልሱ በዝምታ መመልከቱ ከአንድ መንግስት የማይጠበቅ ስራ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በየአካባቢው የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ህብረተሰቡ ለመንግስት ቢያቀርብም፣ ጥያቄውን ባቀረቡ ሰዎች ላይ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን ግልጸዋል፡፡