ኢሳት (መጋቢት 30 ፥ 2008)
የህወሃት አገዛዝ ከ15ሺ የሚበልጡ አዳዲስ ሰፋሪዎችን በወልቃይት አካባቢ ሊያሰፍር መሆኑ ተሰማ።
በሰሜን አሜርካ የወልቃይት ማህበረሰብ ተወካይ አቶ ቻላቸው አባይ እንደተናገሩት፣ የህወሃት መንግስት የጎንደርን ታሪካዊ መሬት በጉልበት ከወሰደ በኋላ በህዝቡ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ኣየፈጸመ ነው ብለዋል።
“የወልቃይት የማንነት ጥያቄ፣ የፌዴራሊዝምን ስርዓት የሚንድ በመሆኑ በቀላሉ ልናየው አይገባም” የሚል መረጃ የህወሃት ደህንነቶች በኩል እያሰራጩ እንደሆነ የገለጹት አቶ ቻላቸው፣ ህወሃት ከዚህ በፊት ከትግራይ በማምጣት ካሰፈራቸው ከ60ሺ በላይ ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች 15ሺ የሚሆኑ ሰፋሪዎችን በወልቃይት ለማስፈር እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሰፋሪዎቹ የታጠቁ ሚሊሺያዎች ስለሆኑ ሰፋሪም ጦረኛም ሆነው ለማገልገል የተዘጋጁ ናቸው ተብሏል።
በቅርቡ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍም ትግሬ እንጂ አማራ አይደለም ብሎ ያሰለፋቸው ሰዎች ከዚህ በፊት በሰፈራ መልክ ወደ ወልቃይት የመጡ የትግራይ ተወላጆች መሆናቸውን አቶ ቻላቸው ለኢሳት ገልጸዋል።
ሆኖም የህወሃት አገዛዝ ከፍተኛ የአፈና እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ቢቀጥልም፣ የወልቃይት-ጠገዴ-ጠለምት ህዝብ በአንድነት ከመቼውም በበለጠ ማንነቱን ለማስከበር ከአማራ ህዝብ ጋር በጋራ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ታውቋል።
የወልቃይት አማራ የማንነት ኮሚቴዎች፣ በወልቃይት ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም አማራ ክልል ህዝቡን እያነጋገሩና እያወያዩ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል። በመሆኑም በወሎ እስከ ራያ በጎጃም እስከ መተከል አካባቢ ድረስ በግፍ የተወሰደው የወልቃይት-ጠገዴ-ጠለምት መሬት ጉዳይ ህዝቡን እያነጋገረ እንደሆነ አቶ ቻላቸው ለኢሳት ተናግረዋል።
የኮሚቴው አባላት ባለፈው ሳምንት ጎንደር ከተማ ከህብረተሰቡ ጋር ስለ ወልቃይት-ጠገዴ-ጠለምት ማንነት ጉዳይ ላይ መወያየታቸውና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እንደተገኘ ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። ችግሩን በማስመልከትም የጠለምት ተወካዮችም በጉዳዩ ላይ መግለጫ ማውጣታቸው ይታወቃል። በወልቃይት ጉዳይ ላይም ቀጥተኛ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።
መብታችን ነው ብለው የሚንቀሳቀሱ የመፍትሄ የወልቃይት ጠገዴ አማራነት ኮሚቴ አባላት ከህወሃት የደህንነት አባላት ማስፈራሪያና ወከባ እየደረሰባቸው ቢሆንም፣ የኮሚቴው አባላትና በወልቃይት ጠገዴ የሚኖሩ ህዝቦች፣ የራሳችንን ማንነት ከምናጣ፣ እስከ ህይወታችን ፍጻሜ የሚደርስ የሚችል መስዋዕትነት ሊከፍሉ እንደተዘጋጁ ለእሳት ተናግረዋል።
በትግራይ ወገኖችና በወልቃይት አማሮች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር የሚመለከተ አካል ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም በሰሜን አሜሪካ የወልቃይት ማህበረሰብ ተወካይ የሆኑት አቶ ቻላቸው አባይ ተማጽነዋል።