ኢሳት (የካቲት 30 ፥2008)
ትናንት ማክሰኞ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች የተካሄድውን ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥራቸው በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ተማሪዎች ከስድስት ኪሎ ዩንቨርስቲ መታሰራቸው ተገለጠ።
በጸጥታ ሃይሎች ለእስር የተዳረጉት ተማሪዎች ተቃውሞን አስተባብራችኋል ተብለው መጠርጠራቸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለው ግድያና የጅምላ እስራት እንዲበቃ ጥያቄን ያቀረቡት የዩንቨርስቲው ተማሪዎች አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ፊት ለፊት በመሰባሰብ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
ይህንኑ አስገራሚ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎም ማክሰኞ እና ረቡዕ በርካታ ተማሪዎች ከስድስት ኪሎ ዩንቨርስቲ መታሰራቸው ታውቋል።
ያልተጠበቀ ነው የተባለውን ተቃውሞ ለመበተን የጸጥታ ሃይሎች በተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን ሮይተርስ ተማሪዎችን ዋቢ በማድረግ የዘገበ ሲሆን፣ በኢምባሲው ዙሪያ የጸጥታ ቁጥጥሩ መጠናከሩን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሶስተኛ ወሩን ዘልቆ የሚገኘው ይኸው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በተያዘው ሳምንትም በወለጋ ዩንቨርስቲና በሌሎች የክልሉ ከተሞች መቀጠሉንም ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ሂውማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የፓርቲ አመራሮች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ባለው እርምጃ እስካሁን ድረስ በትንሹ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይገልጻሉ።
የመንግስት ባለስልጣናት ከተቃውሞ ጀርባ የተደራጁ ጸረሰላም ሃይሎች አሉ በማለት እርምጃን እንደሚወስዱ ቢያሳስቡም ተቃውሞው አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱ ይታወቃል።