ኢትዮጵያና ሱዳን በድንበር አካባቢ ተቆጣጣሪ ሃይል በሚሰማራበት ሁኔታ መከሩ

ኢሳት (የካቲት 29 ፥ 2008)

ከኢትዮጵያ ጋር ድንበርን ለማካለል በዝግጅት ላይ የምትገኘው ሱዳን በሁለቱ ሃገራት የድንበር አካባቢ የጋራ ድንበር ተቆጣጣሪ ሃይል እንዲመሰረት አዲስ ሃሳብ አቀረበች።

የኢትዮጵያና የሱዳን መከላከያ ሚኒስትሮች በዚህና ተጓዳኝ ጉዳዮች ዙሪያ በሱዳን መዲና ካርቱም መምከራቸውን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ዘግቧል።

የሱዳኑ መከላከላይ ሚኒስትር አዋድ ኢብን ኡፍ በሁለቱ ሃገራት መካከል በጋራ ሊቋቋም የታሰበው ሃይል የሁለቱን ሃገራት ጥቅም እንደሚያስጠብቅና በድንበሩ ዙሪያ ቁጥጥርን እንደሚያካሄድ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ሁለቱ ሃገራት ከአመት በፊት ድንበራቸውን ለማካለል የደረሱበትን ስምምነት ተከትሎ በድንበሩ ዙሪያ ተከታታይ ምክክሮች ሲያካሄዱ መቆየታቸው ይታወቃል።

ሰኞ በካርቱም የተካሄደው የዚሁ አካል ምክክርም በድንበሩ ዙሪያ ያሉ የመግባቢያ ነጥቦችን አንስቶ የመከረ ሲሆን የሁለቱ ሃገራት ወታደራዊ ተወካዮች የልምድና የወታደራዊ ስልጠናዎች ለማካሄድ ስምምነት ማድረጋቸውንም ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ሲራጅ ፈርጌሳ በበኩላቸው ከሱዳኑ የጋራ ኮሚቴ ጋር ያደረገቻቸው ስምምነቶች ተግባራዊ እንደምታደርግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያና የሱዳን ባለስልጣናት ድንበርን ለማካለል የሚረዳ ስምምነት መፈረማቸውን ተከትሎ በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች በሱዳን የጸጥታ ሃይሎች መሬትን ልቀቁ የሚል ዛቻ ሲደርስባቸው መቆየቱን ለኢሳት መግለጻቸውም  ይታወሳል።

በአማራ ክልል ድንበር ዙሪያ የሚገኘው አል-ፋሻጋ አካባቢ ለዘመናት በኢትዮጵያ ስር ሲተዳደር መቆየቱን የሚናገሩት ነዋሪዎች ስምምነቱን ተከትሎ የሱዳን ወታደሮች ስፍራውን ለሱዳን ተሰጥቷት የሚል ምክንያትን እንደሚያቀርቡ ይገልጻሉ።

በሁለቱ ሃገራት መካከል የተፈረውምን የድንበር ማካለል ስምምነት ተከትሎ ኢትዮጵያውያንና የታሪክ ምሁራን ስምምነቱ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ ነው በማለት ተቃውሞን ማሰማታቸውም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለሱዳን ጋር የተደረሰ አዲስ ስምምነት የለም በማለት ድርጊቱን እያስተባበሉ የሚገኙ ቢሆንም የሱዳን ባለስጣናት ድንበሩ በቅርቡ እንደሚካለል በተደጋጋሚ ይፋ አድርገዋል።