የካቲት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት አሽከርካሪዎችን በተመለከተ ያወጣው ህግ የሚያሰራ አይደለም በማለት ፣ በህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ሾፌሮች፣ የጀመሩት አድማ ለሶስተኛ ቀን ቀጥሎአል። ሾፌሮቹ ዛሬ ወደ ደብረታቦር ከተማ በመሄድ ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ቢነጋገሩም ፣ ባለስልጣናቱ አድማ ላደረጋችሁበት 1 ሺ ብር ቅጣት ካልከፈላችሁ ስራ አትጀምሩም በማለታቸው፣ ተበሳጭተው መመለሳቸውንና በአድማው ለመቀጠል መወሰናቸውን ለኢሳት ተናግረዋል።
ከደብረታቦር ሲመለሱ መንገድ ላይ ያነጋገርናቸው አሽከርካሪዎች፣ “ጥያቄያችን ነጻነት ነው፣ ነጻነት እንፈልጋለን፣ እባካችሁ አስታጥቁን፣ መሮናል” በማለት በከፍተኛ ቁጭት ተናግረዋል።
በአደማው የጋይንት እና የደብረታቦር ሾፌሮች አብረው ቢሳተፉም፣ ትናንት ከሰአት በሁዋላ ስራ ጀምረዋል። በሁለቱ ከተሞች ሾፌሮች ላይ ቅጣት አለመጣሉም ታውቋል።
በሌላ በኩል በአካባቢው በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት መሰማራታቸውን ለማወቅ ተችሎአል።