የካቲት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ትናንት ከሰዓት በሁዋላ በወልድያ የተጀመረው የታክሲ እና አውቶቡስ አሽከርካሪዎች አድማ በደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ውርጊሣ፣ ውጫሊ ቆቦ እና አላማጣ መስመሮችም እየተካሄደ ነው።
በወልድያ ዛሬ የከተማው ባለስልጣናት ታርጋ ሲፈቱና ባለሀብቶችን ሰብስበው ሲያነጋግሩ አርፍደዋል። ባለሃብቶቹ ሾፌሮቻቸውን መክረው ስራ እንዲያስጀምሩ ፣ ስራ ካልቸጀመሩ ግን እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ባለስልጣናቱ ለማስፈራራት ቢሞክሩም፣ ባለሀብቶቹ ግን ” የምትፍልጉትን አድርጉ፣ የወሰዳችሁትን ታርጋም መልሱ፣ የሹፌሮችን ጥያቄ ሳትመልሱ ቁልፍ አንሰጣቸውም።” የሚል መልስ ሰጠዋል። የአማራ ክልልን የፖሊሲያችሁ መሞከሪያ አድርጋችሁታል፤ እንደ እንስሳ ቆጥራችሁናል፣ ከእንግዲህ ግን በቃ በማለት ባለሀብቶች በአንድነት ተናግረዋል።
ደሴ መናሀሪያና እና ከደሴ ኮምቦልቻ የሚወስደው መስመር ጭር ብሎ የዋለ ሲሆን፣ አድማው በሌሎችም የክልሉ ከተሞች ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው ሰኞ ተመሳሳይ የአሽከርካሪዎች አድማ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወቃል። መንግስት ያወጣው አዲስ የትራፊክ ህግ ፣ ህጉን በሚጥሱት ላይ ከባድ ቅጣቶችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ሾፈሮች “ህጉ በሙስና ለተዘፈቁት የትራፊክ ፖሊሶች የሚስማማና ከስራ ውጭ የሚያደርገን ነው” በማለት ይቃወማሉ።