ኢሳት (የካቲት 18 ፥2008)
በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ዳግም ያገረሸው ህዝባዊ ተቃውሞ አርብ ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ወሊሶ መዛመቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች በከተማዋ የተዘረጋን ዋና መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ ሲያቀርቡ መዋላቸው ታውቋል።
በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ አካባቢዎች በሚገኙ የገጠር ከተሞች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አርብ የቀጠለ ሲሆን ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በምዕራብ ሸዋ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች እንዲሁም በምዕራብ ወለጋ መካሄዳቸውን ለመረዳት ተችሏል።
የፀጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ለመቆጣጠር በወሰዱት እርምጃም በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ቁጥራቸው ሊይታወቅ ያልቻለ ሰዎችም መገደላቸውን ነዋሪዎችና የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞን ለመቆጣጠር የተጀመረው የሃይል እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ላይ ቢሆኑም ተቃውሞ ተቃውሞው ወደ አዳዲስ አካባቢዎች በመዛመት ላይ መሆኑ ተነግሯል።
በክልሉ በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች የፀጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ባለው የሃይል እርምጃ ፍርሃትና ጭንቀት አድሮባቸው እንደሚገኝ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ሃሙስ መዘገቡ ይታወሳል።