የካቲት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህወሃት የሚመራው የትግራይ ክልል፣ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ የሚያቀርቡ ግልሰቦችን የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎችን ዛሬም በሁመራ ከተማ አዘጋጅቷል።
ይኸው በክልሉ መንግስት የሚቀነባበረው የተቃውሞ ሰልፍ፣ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የአማራ ማንነቱ ይከበርለት በማለት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥያቄውን እንደገና ባነሱት የወልቃይት ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ነው። የወልቃይትን ህዝብ ተወካዮች ” ማንነታቸው ከአማራ ህዝብ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ፣ መብታችን ተከብሮልን ወደ አማራ ክልል እንጠቃለል በማለት ጥያቄያቸውን ለፌደራሉ መንግስት አቅርበዋል። ይህ እንቅስቃሴ የሰሜን ጎንደርን ህዝብ ትኩረት ማግኘቱን ተከትሎ፣ የህወሃት ባለስልጣናት ጥያቄ አቅራቢዎችን በማስፈራራት ጥያቄውን ለማዳፈን ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጅ ጥያቄ አቅራቢዎቹ፣ ጥያቄያቸውን በማስፈራሪያ እንደማይተው መግለጻቸውን ተከትሎ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ወደ አካባቢው በመሄድ ህዝቡን ሰብስበው ጥያቄ አቅራቢዎች እንዲወገዙ ካደረጉ በሁዋላ፣ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎችን በማድረግ፣ የትግራይ ህዝብ የውግዘቱ አካል እንዲሆን እያደረጉት ነው።
በሁመራ ለተቃውሞ የወጡት ነዋሪዎች፣ ” የማንነት ጥያቄ ተከብሮ የቆየ እንጅ እንደ አዲስ የሚነሳ አይደለም” የሚል መፈክር ይዘው ቢወጡም፣ የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ፣ አገሪቱ በክልል ከተካለለችበት ጊዜ ጀምሮ ሲንከባለል የቆየና፣ ከ300 በላይ የወልቃይት ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ እንዲሁም ብዙዎችን ለስደት የዳረገ ጉዳይ መሆኑን የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጿል።
ህወሃት ያለውን ስልጣን ተጠቅሞ ለእርሻ ተስማሚ የሆነውን አካባቢ ወደ ትግራይ መከለሉ በአካባቢው ለሚፈጠረው ተደጋጋሚ አለመረጋጋት አንድ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
ህወሃት የወልቃይትን ትግራዋይነት ለሚደግፉት ሰላማዊ ሰልፍ የሚፈቅድ ከሆነ፣ የአማራ ማንነታችን ይከበርልን ለሚሉትም የተቃውሞ ሰልፍ ሊፈቅድ ይገባል በማለት የወልቃይት ተወላጆች እየጠየቁ ነው።
መንግስት የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ በሻእቢያና በአርበኞች ግንቦት7 የሚቀነባበር ነው በማለት ክስ ማሰማቱ ይታወቃል። ይሁን እንጅ ጥያቄውን የሚያቀረቡት አብዛኞቹ ሰዎች፣ በትጥቅ ትግል ወቅት ከኢህአዴግን ጎን ተሰልፈው ሲዋጉ የነበሩ ናቸው። ጥያቄ አቅራቢዎቹ ብአዴን ጥያቄያቸውን ደግፎ እንዲቆም ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ብአዴን በወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ዙሪያ እስካሁን አቋሙን ግልጽ አላደረገም።