የካቲት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ምንጮች እንዳሉት በተለያዩ የውስጥ ችግሮች ተወጥሮ የሚገኘው ኢህአዴግ በኤርትራ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በአካባቢው በሚገኙ የመንግስት ወታደሮች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ወጣቶችም እነዚህን ነጻ አውጭዎች ለመቀላቀል ድንበር አቋርጠው እየተጓዙ ነው። ይህ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ስጋት ላይ የጣለው የኢህአዴግ መንግስት፣ በኤርትራ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ለመክፈት ወታደራዊ ልምምዶችንና ዘግጅቶችን በማድረግ ላይ ነው።
ሰሞኑን በኦሮምያ ለተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ የኤርትራ እጅ አለበት ሲሉ አቶ ሃይለማርያም መናገራቸው ይታወሳል።
ምንም እንኳ የተፈለገውን ያክል የሰው ሃይል ባይገኝም፣ ኢህአዴግ መንግስት ሁለተኛ ዙር ወታደራዊ ምልመላ ለመጀመር ማስታወቂያዎችን በየቦታው ለጥፏል።
መከለከያ ሰራዊቱ በከፍተኛ ሁኔታ በዘር ተከፋፍሎ በሚገኝበት በዚህ ወቀት ፣ በኤርትራ ላይ ጥቃት መፈጸም፣ የኢህአዴግን ፍጻሜ ያፋጥነዋል በማለት ምንጮች አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
በኢትዮጵያ በኩል የሚደረገውን የጦር ዝግጅት በተመለከተ የኤርትራ መንግስት የሰጠው መግለጫ የለም።