የካቲት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በምእራብ አርሲ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ተቃውሞው ተጠንከሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በዶዶላ ትናንት እና ዛሬ በነበረው ተቃውሞ ከ10 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል። ሆስፒታል በርካታ ሰዎች ተመትተው የተኙ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በህይወት የመትረፍ እድላቸው አነስተኛ ነው ተብሎአል። ትናንት በነበረው ተቃውሞ የሞቱ 2 ሰዎችን ለመቅበር የወጣው ህዝብ፣ ሟቾቹን መቅበር አትችሉም በመባሉ፣ ተቃውሞውን ጀምሯል። መብታችን ይከበር፣ የታሰሩት ይፈቱ፣ ለተገደሉት ካሳ ይከፈል የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች በማሰማት ተቃውሞውን ሲቀጥል፣ የአጋዚ ወታደሮች በወሰዱት የአጸፋ እርምጃ 4 ሰዎች መቁሰላቸው ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ከተማው ቀኑን ሙሉ በተኩስ ስትናወጥ የዋለች ሲሆን፣ የእለቱ ገበያም ሳይካሄድ ቀርቷል። ሌሊት ላይ የሁለት የግለሰብ ቤቶች እና አንድ ባቡር ቤት ተቃጥለዋል። አንደኛው ግለሰብ ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያለው ነው ተብሎአል።
በአሰሳም ተቃውሞው ቀጥሎ መዋሉን ለማወቅ ተችሎአል። የምእራብ ወለጋ ኪማ አርጆ መንገድም በተቃውሞው የተነሳ ተዘግቶ ውሎአል። ማምሻውን በደረሰን ዜና አንድ የ2ኛ ክፍል ተማሪ እድሜዋ 7 ወይም 8 አመት የሚሆናት ሴት ልጅ በአጋዚ ወታደሮች ተገድላለች። በጉደር፣ አምቦም እንዲሁ ህብረተሰቡ ድንጋይ በመዝጋት ተቃውሞውን ገልጿል።
በክልሉ ውስጥ የፌደራልና የመከላከያ አባላት በብዛት የተሰማሩ ሲሆን፣ በአርሲ የሚገኙ የልዩ ሃይል አባላት ትጥቅ ሊፈቱ ይችላሉ የሚሉ ወሬዎች እየተናፈሱ ነው። አንዳንድ የልዩ ሃይል አባላት ከህዝቡ ጎን በመቆም፣ በአጋዚ ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረስ መጀመራቸው ታሰምቷል።
በአዳባ የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች፣ ከኦሮሞ ብሄር ውጭ ያሉ ዜጎችን ቀርበው በማናገር እንደረጋጉና የገዢው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ እንዳይሆኑ ምክር በመለገስ ላይ መሆናቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። አገር ሽማግሌዎቹ፣ “በእናንተ ላይ የሚመጣ ጥቃት በእኛ ላይ እንደመጣ እንቆጥረዋለን” በማለት የሌሎች አካባቢ ሰዎች ሳይደናገጡ ትግሉን እንዲደግፉ በማግባባት ላይ ናቸው።