ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2008)
ባለፉት ሶስት ወራቶች ብቻ በደረሱ የትራፊው አደጋዎች ከ1ሺ 100 በላይ ሰዎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች መሞታቸውን የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጠ።
ይኸው ቁጥር በአመቱ መጨረሻ 4ሺ 600 ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅና፣ በሃገሪቱ እየደረሰ ያለው የትራፊክ ጉዳት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ሚኒስትሩ ማስታወቁን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ በሃገሪቱ በአመት 2ሺ 500 ሰዎች ይሞቱ የነበረ ቢሆንም ቁጥሩ እየጨመረ መጥቶ ወደ 5ሺ አካባቢ በመድረስ ላይ መሆኑን ከሚኒስትሩ የተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ከመስከረም ወር እስከ ታህሳስ 2008 አ ም በደረሱ 813 የትራፊክ አደጋዎች 1156 ሰዎች መሞታቸውም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ካላት ተሽከርካሪ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በሃገሪቱ በህይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው አደጋ ከሌሎች ሃገራት ጋር ሲወደደር ከፍተኛ መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
በሃገሪቱ ያለው ተሽከርካሪ ግማሽ ሚሊዮን ባይሞላም በአመት በአማካይ እስከሶስት ሺ ሰዎች ሲሞቱ መቆየታቸውንም ከድርጅቱ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።