ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2008)
የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው ልዩ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ተከትሎ በመዲናው በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል መሰማራቱን ነዋሪዎች ገለጡ።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ካለው የጸጥታ ቁጥጥር በተጨማሪ በሰበታ፣ ጫንጮና አካባቢዋ ባሉ የገጠር መንደሮች የጸጥታ ሃይሎች መሰማራታቸው ታውቋል።
በእነዚህ አካባቢዎች ባለፈው ወር ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲካሄድባቸው የነበረ ሲሆን ተመሳሳይ ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በመዲናዋ አዲስ አበባ ማንኛውም አይነት ህዝባዊ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ መደረጉን የተናገሩት ነዋሪዎች የጸጥታ ቁጥጥሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሁለተኛ ወሩን የዘልቀው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ለጸጥታ ቁጥጥሩ መጠናከር ምክንያት መሆኑንም ስማቸው መግለጽ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አስረድተዋል።
በመዲናዋ በተለያዩ ቦታዎች ተሽከርካሪዎች እንዲቆሙ ተደርጎ ፍተሻ እየተካሄደ እንደሆነም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችም ፍተሻ እየተካሄደባቸው የሚገኝ ሲሆን የጸጥታ ሃይሎች መንገደኞችን መታወቂያ እንደሚጠይቁ ከነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፣ ጉባዔው የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል መሰማራቱን ገልጿል።