ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሳሳቢ የሆነ የምግብ አቅርቦት እጥረት አጋጥሟቸው እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሃሙስ አስታወቀ።
በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥም ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ የእርዳታ አቅርቦት የማይገኝ ከሆነ በርካታ ተረጂዎች ህይወታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ድርጅቱ መግለጹን ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ ዘግቧል።
የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ወቅታዊ ምላሽ ባለማድረጉ የተረጂዎች የእለት ከእለት የጤንነትና የአካል ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ማስተባበሪያ ቢሮ በድጋሚ አስታውቋል።
አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ቢገልፁም በእስካሁኑ ሂደት ከአንድ አራተኛ ያነሰ ገንዘብ ብቻ ሊገኝ መቻሉ ታውቋል።
ይኸው በስድስት ክልሎች በሚገኙ ከ180 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳትን ኣያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ በተያዘ የፈረንጆች አመት ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል ሲል አንድ የጣሊያን የበጎ አድራጎት ተቋም በቅርቡ ማሳሰቡ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ ተረጂዎች ወቅታዊ ድጋፍ እያገኙ ባለመሆኑ የበርካታ ሰዎች ህይወት አደጋ ሊያጋጥመው እንደሚችል ሃሙስ አሳስቧል።
በተለይ በድርቁ ሳቢያ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው የግማሽ ሚሊዮን ህጻናት ጉዳይ ቀጠሮ የማይፈልግ ችግር ሆኖ መገኘቱ ድርጅቱ አመልክቷል።
ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ህጻናት ሲሆኑ ከእነዚሁ መካከል ግማሽ ሚሊዮን ክፉኛ የምግብ እጥረት ጉዳት እያደረሰባቸው ይገኛል።
የህጻናቱ ህይወት ለመታደግ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርጉም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪውን አቅርቧል።
በአዲስ አበባ ከተማ የተሰባሰቡት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አባል ሃገራት መሪዎች በኢትዮጵያና በሌሎች ጥቂት የአፍሪካ ሃገራት ተከስቶ ላለው የድርቅ አደጋ ጥሪውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የድርቁ አደጋ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ተከትሎ የህጻናት ጋብቻ እየጨመረ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
በተለይ በቤተሰብ ደረጃ ድርቁ ያደረሰውን ችግር ለመቋቋም ሲሉ በርካታ ቤተሰቦች ሴት ህጻናት ልጆቻቸውን ያለእድሚያቸው እየዳሩ መሆኑን ድርጅቱ ባካሄደው ጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል።
በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሊ፣ እና ትግራት ክልሎች የተካሄደው ይኸው ጥናት በርካታ ወላጆች የህጻናቱን ህይወት ለመታደግ ሲሉ ያለ እድሚያቸው ለጋብቻ እያበቋቸው እንደሆነ በሪፖርቱ አመልክቷል።
የችግሩ አሳሳቢነት በመረዳትም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለህጻናቱ ልዩ ጥበቃና ከለላ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያካሄደ እንደሚገኝም ገልጿል።
ይሁንና ለዚሁ የድርቅ አደጋ ሳቢያ ምን ያህል ህጻናት ለጋብቻ እንደተዳረጉ ድርጅቱ የገለጸው ነገር የሌለ ሲሆን አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ህጻናትን ለመታደግ አለም አቀፍ ርብርብ እንዲደረግ በማሳሰብ ላይ ናቸው።