ኢሳት (ጥር 19 ፥ 2008)
ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች በመገደብ ነጻ ካልሆኑ አገራት መመደቧን ፍሪደም ሃውስ የተሰኘ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋም ዛሬ ባወጣው አመታዊ ሪፖርት ገለጸ።
ፖለቲካዊ መብቶችን እና የሲቪል ነጻነትን አስመልክቶ የተሰራው ይኸው የዘንድሮው 2016 የፍሪደም ሃውስ ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ የዜጎችን ፖለቲካዊ መብቶችን በመጨፍለቅ ቀዳሚ አገር እንደሆነች በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል። በተመሳሳይ መልኩም የዜጎችን ነጻነት ካለፈ አመት በባሰ መልኩ እጅግ እንደተሸረሸረ ረፖርቱ ያብራራል።
የፕሬስና የበይነ-መረብ ነጻነትን ጨምሮ የዳሰሰው ይኸው የፍሪደም ሃውስ የ2016 ዘገባ፣ ኢትዮጵያ በዜጎች ነጻነት፣ በፕሬስ እና በበይነመረብ ነጻነት “ነጻ ያልሆኑ አገራት” ጎራ ውስጥ እንደተመደበች ታውቋል። ኢትዮጵያ የተራቀቀ ሳንሱር፣ የመረጃና ፕሮፓጋንዳ ቁጥጥር እንደምታደርግና ተቃዋሚዎችን ለመጨፍለቅ የተለያዩ ህጎች እንደምትጠቀም ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያ የዜጎችን የፖለቲካና የሲቪል ነጻነቶችን ለመግፈፍ የተለያዩ ህጎችን አውጥታ በስራ ላይ እያዋለች እንደሆነ ዘገባው አክሎ ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ የ“ጸረ-ሽብርተኛ ህግ” በመጠቀም የዜጎችን የእለት ተዕለት ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ እንደምትጠቀም ረፖርቱ ያትታል።
የፍሪደም ሃውስ የኢትዮጵያ መንግስት ሃይሎች በማስተር ፕላን ላይ ተቃውሞ በወጡ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያና፣ እስርና ወከባ እንደፈጸሙባቸውና፣ የጸረ-ሽብር ህጉን በመጠቀም ተቃውሞውን ለማስቆም እየሞከሩ መሆኑን በዘገባው አመልክቷል። በተጨማሪም የኢህአዴግ መንግስት የጸረ-ሽብር ህጉን እንደሽፋን በመጠቀም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን፣ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንን፣ እና አክቲቪስቶችን በማሰር እና በማዋከብ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል።
በስልጣን ላይ ያለው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እቅድ ተቋርጧል ቢልም የአርሶ አደሮች ከመሬታቸው መፈናቀል ያሳሰባቸው ዜጎች ግን ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሟቾች ቁጥር በትንሹ 140 መድረሱን ቢገልጹም ተቃውሞው ባለመቆሙ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።