ጥቅምት 29 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- “ከኢትዮጵያ ጋር የቆየና የሰነበተ የረዥም ጊዜ ግንኙነት አለን፤ይህ ግን በኢትዮጵያ እየታየ ስላለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዝም እንድንል የሚያደርገን አይደለም” ሲሉ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት አስታወቁ።
የምክር ቤት አባላቱ ይህን ያስታወቁት በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በሰጡት ወቅት ነው። የሊበራል ፓርቲ ተወካዩዋ ወይዘሮ ማርቲና ሹስተር ኢትዮጵያ አዲስ ባወጣችው የፀረ-ሽብር ህግ ሽፋን ከመንግስት የተለየ አስተሣሰብ የሚያራምዱና በስርዓቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሁሉ እየታሰሩ ነው ብለዋል።
“ህግ ይፈቅድልኛል እያሉ አንድን ሰው ያለወንጀሉ በዘፈቀደ ማሰር ፈጽሞ አይቻልም”ያሉት ወይዘሮ ሹስተር፤ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች በህግ ሽፋን እየታሰሩ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ
አመልክተዋል።
“በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ነገር እኛን ሊበራሎቹን እጅግ ያሣስበናል”ያሉት ወይዘሮ ሹስተር፤በአገሪቷ ለጋዜጠኞች፣ለተቃዋሚዎችና ለኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ያለው ነፃነት ወደ ፊት ከመሄድ ይልቅ፤ ወደ ሁዋላ
ተመልሶ ቀጭጮ ቀርቷል ብለዋል።
የሊበራል ፓርቲ ተወካዩዋ “ማስፈራራት በአገሪቷ ላይ ነግሷል።ያነጋገርኳቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ድርጅቶች ሌላው ቀርቶ የሚገናኙበትና የሚሰባሰቡበት እንኳ ቢሮ የላቸውም ።የመንቀሳቀሻ ገንዘብና የመገናኛ መስመርም እንደዚሁ የላቸውም።ከሁሉም በላይ መንግስት እየሰራ ስላለው ሥራ ለመጠየቅ፣ለመወያየትና ለመነጋገር ምንም ዓይነት ዕድልና መንገድ የላቸውም” ሲሉም ተናግረዋል የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ህግ ከሌሎች አገሮች የፀረ-ሽብር ህግ የተለየ እንደሆነም ወይዘሮ ሹስተር ሳይጠቁሙ አላለፉም።
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር ታስቦ የወጣውም ህግ እንዲሁ በአገሪቱ ዲሞክራሲን ለማስፈን የሚደረግን ሙከራ የሚያደናቅፍ እንደሆነ የህዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል።
“ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ግንኙነት ስላለን ብቻ፤በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝን አስመልክቶ እየተፈፀመ ያለውን ነገር ችላ የምንለው አይደለም”ሲሉም አባላቱ ተናግረዋል።
ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት እንዳላት ይታወቃል።