ጥር ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ፣ በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን በመገናኛ ብዙሃን ባስታወቀ ማግስት በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ተቃውሞዎች ተነስተዋል። የተቃውሞዎች ዋነኛ አጀንዳ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ስረዛ ወደ ሌሎች የመብት ጥያቄዎች ተሸጋግሯል። በጉጂ ፣ ሰሜን ሸዋና ምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ በተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች፣ ነዋሪዎች የታሰሩት እንዲፈቱ፣ ለወራት በዘለቀው ተቃውሞ ግድያ፣ ድብደባና ሰቆቃ የፈጸሙ ወታደሮችና አዛዦቻቸው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ክልሉን ለቆ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
መንግስት የአገር ሽማግሌዎችን በማናገር ተቃውሞው እንዲበርድ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያድርግም፣ ተቃውሞውን ለማብረድ አልቻለም። በአንዳንድ አካባቢዎች ነዋሪዎች ኦህዴድ አይወክለንም የሚል መፈክር ሲያሰሙ ተሰምተዋል።
ለሁለት ወራት ያክል በዘለቀው ታሪካዊ በተባለው ተቃውሞ ከ150 በላይ ዜጎች በመንግስት ወታደሮች ተገድለዋል።ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ቆስለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ታስረዋል።
የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ግድያውን አውግዘዋል። ጋዳዮችም ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
ኦህዴድ ለተቃውሞው መነሻ ነው የተባለውን አዲስ አበባ ማስተር ፕላን መተውን ማስታወቁ ይታወሳል። የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ተቃውሞው ማስተር ፕላኑን ሰበብ አድርጎ ቢነሳም፣ የህዝቡ ጥያቄ ግን ሌሎች መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎችን ያካተተ ነው።