አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ተቋርጠው የነበሩት ከ80 በላይ የሚሆኑ ክሶች እንደገና እንዲታዩ ተወሰነባቸው

ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)

ከመንግስት ጋር ያደረጉት ስምምነት ተከትሎ በቅርቡ ወደሃገር የተመለሱትና ከቀናት በፊት ለእስር የተዳረጉት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራች የተቋረጡባቸው ከ 80 በላይ ክሶች እንደገና እንዲታዩ ተወሰነ።

የኩባንያው መስራችና አመራር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ወደሃገር ከተመለሱ በኋላ ሊተገብሩ ቃል የገቡትን ስራ ባለማከናወናቸው ምክንያት ክሳቸው እንዲቀጥል መደረጉን የፍትህ ሚኒስቴር ገልጿል።

ከመንግስት ጋር ድርድር አድርገው ባለፈው አመት ወደሃገር ቤት የተመለሱት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራች፣ ወደሃገር ሲመጡም ያለመታሰር ዋስትና አልተሰጣቸውም ነበር ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጻቸው ከሃገር ቤት የተገነው መረጃ አመልክቷል።

የገቡትን ቃል መፈጸም አልቻሉም የተባሉ አቶ ኤርሚያስ ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር መዋላቸው የሚስታወስ ሲሆን፣ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ እና የተቋረጡ ከ80 በላይ ክሶችም እንደገና የሚታዩ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

አክሰስ ሪል ስቴስ ከስድስት አመት በፊት ከሁለት ሺ በላይ ከሚሆኑ ደንበኞች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ወደስራ ቢገባም ለደንበኞቹ መኖሪያ ቤትን አላስረከበም በሚል ብውዝግብ ውስጥ መቆየቱ ይታወቃል። አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በበኩላቸው ቤቶቹን ሰርቶ ለማስረከብ የገጠማቸው መሰናክልም መግለጻቸው ይታወሳል።