በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ሰበብ እየሞቱ ያሉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው ተባለ

ኢሳት (ጥር 6 ፥ 2008)

ሁለተኛ ወሩን በያዘው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ፣ በየዕለቱ የሚገደሉ ሰዎችና ለእስር የሚዳረጉ ተማሪዎች ቁጥር በማሻቀብ ላይ መሆኑ ሂውማን ራይትስ ዎች አርብ ጃንዋሪ 15 አስታወቀ።

በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ቀጥሎ በሚገኘው በዚሁ ተቃውሞ የሟቾችንም ሆነ ለእስር የተዳረጉ ነዋሪዎችን ቁጥር በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጀት ለሁለተኛ ጊዜ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ሃሙስ ከሌሎች ሁለት አለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጥሪውን ያቀረበው ሂውማን ራይትስ ዎች መንግስት የማስተር ፕላኑ እቅድ ተግባራዊ አይሆንም ሲል ከገለጸ በኋላም ተቃውሞው ቀጥሎ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ባለው እርምጃም በተለይ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በብዛት ለእስር መዳረጋቸው ገልጿል።

በስልጣን ላይ ያለው ገዥው የኢህአዴግ መንግስት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እቅድ ተቋርጧል ቢልም የአርሶ አደሮቹ መፈናቀል በሌሎች ክልሎች እንደታየው ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል ተቃውሞ እያሰሙ ያሉ አካላት ለድርጅቱ አስረድተዋል።

መንግስት ለልማት የያዘው እቅድ ላይ መሰረታዊ ለውጦች የማይተገበር ከሆነም መሰል ተቃውሞዎች ቀጣይ ሊሆኑ እንደሚችል ሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርቱን አስፍሯል።

በበርካታ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ዳግም አገርሽቶ ያለውን ተቃውሞ ለማብረድ ከተፈለገም መንግስት ለእስር የዳረጋቸው ሰዎች በአስቸኳይ መፍታት ይኖርበታል ሲሉ በሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ጉዳዮች አጥኚ (ተመራማሪ) የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ገልጸዋል።

እስረኞችን ከመፍታቱ በተጨማሪ የተፈጸሙ ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም በገለልተኛ አካል ምርመራ መካሄድ እንደሚኖርባቸው ሚስተር ሆንር አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ጨምሮ በርካታ ፓርቲዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በእስካሁኑ የፅጥታ ሃይሎች እርምጃ በትንሹ ከ150 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይገልጻሉ። ወደ 5ሺ የሚጠጉ ሰዎችም ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ እነዚሁ አካላት በተደጋጋሚ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ተቋማቱ የሚሰጡት ቁጥር የተጋነነ ነው ቢሉም የሟቾቹ ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።