ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ህጻናት በድርቁ ሳቢያ ጉዳት እየደረሰባቸው ነው ተባለ

ኢሳት (ጥር 5 ፣ 2008)

ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ህጻናት ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ምክንያት የሆነው የድርቅ አደጋ በ60 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ህጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ የህጻናት አድን ድርጅት (Save the Children) ሃሙስ ገለጠ።

በድርቁ አደጋ ክፉኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ህጻናት ለመታደግም የአለም አቀፍ ማህበረሰብ አፋጣኝ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት የብሪታኒያው የህጻናት አድን ድርጅት መጠየቁን አፍሪካን ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል።

የፊንላንድ፣ ኖርዌይ፣ የአሜሪካ ህጻናት አድን ድርጅቶች በድርቁ የተጎዱ ህጻናትን ለመታደግ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ችግሩ አፋጣኝ ትብብርን እንደሚፈልግ በኢትዮጵያ የብሪታኒያ ህጻናት አድን ድርጅቶች ተወካይ ጆን ግርሃም ለዜና ወኪሉ አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ የእርዳታ ተቋማት ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ህጻናት በድርቁ ሳቢያ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ከ 10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚያስፈልገው የምግብ ድጋፍ አፋጣኝ ባለመሆኑ ህጻናት ክፉኛ የአካልና የጤና ጉዳት እንደደረሰባቸው ድርጅቱ ገልጿል።

በስድስት ክልሎች ተከስቶ ባለው በዚሁ የድርቅ አደጋ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ትምህርታቸውን ያቋረጡ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችም መዘጋታቸው ታውቋል።

በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ የተረጂዎች ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ሊያሻቅብ ተብሎ የተሰጋ ሲሆን የድርቁ አደጋ እስከቀጣዩ እንደሚሆንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቀዋል።