ያለበቂ ካሳ ከገበሬ የሚወሰደው የመሬት ወረራ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ተቃውሞ አባብሷል ተባለ

ኢሳት (ታህሳስ 5 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ከገበሬዎች መሬትን በመውሰድ ያለበቂ ካሳ ለባለሃብቶች ሲሰጥ የቆየው አካሄድ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ተቃውሞ እንዲባባስ ማድረጉን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በተለያዩ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ሃሙስ ዘገበ።

መንግስት ከገበሬዎች የሚፈልገውን መሬት ወስዶ በቂ ካሳና ምላሽ አለመስጠቱ ነዋሪዎችን አስቆጥቶ ተቃውሞው እንዲበረታ አድርጎታል ሲሉ ከአዲስ አበባ ከተማ በ60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አስጎሪ ከተማ የሚገኙ ገበሬዎች ለጋዜጣው አስታውቋል።

ሁለተኛ ወሩን ይዞ የሚገኘው ይኸው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ዳግም አገርሽቶ በበርካታ ስፍራዎች በመካሄድ ላይ መሆኑንም ጋዜጣው በዘገባው አስፍሯል።

የፌዴራልና የክልል ባለስልጣናት ማስተር ፕላኑ እንዳማያካሄድ በመግለጽ ላይ ቢሆንም ተቃውሞ የሚቆም አይመስልም ሲል ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ሃሙስ ጃንዋሪ 14 ለንባብ ባበቃው እትሙ አመልክቷል።

በአንድ ዩንቨርስቲ ውስጥ መምህር የሆኑት ስዩም ተሾመ በበኩላቸው የጸጥታ ሃይሎች የተኩስ እርምጃ መውሰድ እስከሚጀምሩ ድረስ ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ ሲካሄድ መቆየቱን አስረድተዋል።

በህብረተሰቡ ውስጥ የቆዩ የፍትህ ጥያቄዎች በመኖራቸው ምክንያትም በርካታ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ተቃውሞ በመጠቀም ብሶታቸውን እያሰሙ እንደሚገኝም መምህሩ ለጋዜጣው ገልጸዋል።

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት አርሶ አደሮች እንዲሁ፣ ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ያለበቂ ካሳ ክፍያ መሬታቸውን በሃይል በመውሰድ ለባለሃብቶች ሲሰጥ መቆየቱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ጊንጪ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ተቃውሞው ቀጥሎ እንደሚገኝና የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም እማኞች ለዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አስታውቀዋል።

የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተንሰራፍተው መቆየታቸውንና ከሃላፊነታቸው የሚነሱ ባለስልጣናት እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሟቾች ቁጥር በትንሹ 140 መድረሱን ቢገልጹም ተቃውሞው ዳግም በመቀስቀሱ ምክንያት የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ሰሞኑን ዳግም የተቀሰቀሰው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ በምስራቅ ሃረርጌ አካባቢዎችን እና በአምቦ ዩንቨርስቲ መቀጠሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ረቡዕ በአምቦ ዩንቨርስቲ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ አንድ ተማሪ በጥይት ተመትቶ መገደሉንና በርካታ ተማሪዎችም ድብደባ እንደደረሰባቸው ታውቋል።

የጸጥታ ሃይሎች የወሰዱትን እርምጃ ተከትሎም ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን ቀጥለው የሚገኙ ሲሆን በከተማዋ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል አሰማርቶ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።

በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆሙና ለእስር የተደረጉ ተማሪዎችም እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

በአምቦ ዩንቨርስቲ በተቀሰቀሰው በዚሁ ተቃውሞ፣ በርካታ ነዋሪዎች ድብድደባ እንደተፈጸመባቸውና የሟቾች ቁጥርም ሊጨምር ይችላል ተብሎ መሰጋቱን ከሃገር ቤት ከተገኙ መረጃም ለመረዳት ተችሏል።

የመንግስት ባለስልጣናት የተቋረጠው የዩንቨርስቲዎች ትምህርት ለማስቀጠል ጥረት ቢያደርጉም ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን ቀጥሎ እንደሚገኝ ተገልጿል።