ኢሳት (ጥር 5 ፣ 2008)
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጨምሮ ሶስት አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብና የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች በሃገሪቱ እየተካሄደ ስላለው ግድያና የጅምላ እስር በይፋ ምላሽን እንዲሰጡ ጠየቁ።
የጋራ መግለጫን ያወጡት ድርጅቶቹ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን የሃይል እርምጃ ተባብሶ መቀጠሉንና ድርጊቱ ወደ አሳሳቢ ደረጃ መሸጋገሩን ገልጸዋል።
ወርልድ አሊያንስ ፎር ሲቲዝንስ ፓርቲሲፔሽን (World Alliance for Participation) ኢስት ኤንድ ሆርን ኦፍ ኣፍሪካ ሂማን ራይትስ ዲፌንደር (East and Horn of Africa Human Rights Defender) እና አምነስት ኢንተርናሽናል (Amnesty International) በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን ተቃውሞ በማስመልከት ሃሙስ የጋራ መግለጫን በማውጣት ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጥሪን አቅርበዋል።
መንግስት ሰላማዊ ሰልፈኞችን ሽብርተኛ ብሎ መረፈጁ የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱትን እርምጃ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረጉን ድርጅቶቹ በጋራ ገልጸዋል።
የለአም አቀፍ ማህበረሰብ በሃገሪቱ ስለተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂነት የሚኖርበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባውም ሶስቱ ተቋማት አሳስበዋል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካ ዳይሬከተ የሆኑት ሙቶኒ አንየኪ ሰላማዊ ጥያቄን ያቀረቡ የነበረኡ ሰዎች ሽብርተኛ ተብለው ከተፈረጁ በኋላ የግድያ፣ የእስርና የድብደባ ተግባራት በሰፊው መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ለእስር የተዳረጉ ሰዎችን ቁጥር በትክክል ማወቁ አስቸጋሪ መሆኑን የገለጹት ሶስቱ አለም አቀፍ ተቋማት ታሳሪዎቹ የህግ አገልግሎት እንዳያገኙ ከመደረጉ በተጨማሪ የስቃይ ሰለባ ሊሆኑ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም አስረድተዋል።
በጸጥታ ሃይሎች የተፈጸሙ የሃይል እርምጃዎችን የሚመረምር ገለልተኛ አካልም በአስቸኳይ ተቋቁሞ ግድያውንና እስራቱን እንዲመረምር የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጠይቀዋል።
የሚቋቋመው ገለልተኛ አካል ከመጠን ያለፈ ሃይል ስለመፈጸሙ ካረጋገጠም ለድርጊቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍትህ እንዲቀርቡ ጥሪያቸውን ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ያቀረቡት ተቋማት አክለው ገልጸዋል።