በአማራ ክልል ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር በተገናኘ 200 የሚጠጉ አመራሮች ከስልጣን ተነሱ

ኢሳት (ጥር 4 ፥ 2008)

በአማራ ክልል ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ በህብረተሰቡ ላይ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ወደ 200 የሚጠጉ አመራሮች ከስልጣን ተነሱ።

በክልሉ በሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎች እንዲሁም ቀበሌዎች ውስጥ በተለያዩ መንግስት ሃላፊነት በማገልገል ላይ የነበሩት እነዚሁ ሃላፊዎች ከአመራርነታቸው እንዲነሱ ከተደረጉ በኋላ ጉዳያቸው ወደህግ መወሰዱንም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ከተደረጉት መካከል 90 የሚሆኑንት በድርቅ ለተጎዱት ሰዎች የሚሰጥ ድጋፍን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ሲሉ የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ንጉስ ጥላሁን ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ስድስት የዞን አመራሮች በተካተቱበት በዚሁ ድርጊት አብዛኞቹ አመራሮች መሬትን ጨምሮ የመንግስት ንብረትን በግል ጥቅም አውለዋል ተብሏል።

ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ ከተደረጉት አመራሮች መካከል ሁለት ዳኞች የሚገኙበት ሲሆን የክልሉ መንግስት የወሰደው እርምጃ ከዚህ በፊት ከተወሰዱት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሆኑን ታውቋል።

በቅርቡ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰን ተቃውሞ ተከትሎ የክልሉ ባለስልጣናት በተመሳሳይ እርምጃ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል።