ኢሳት (ጥር 4 ፥ 2008)
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች የተቀናጀ ማስተር ፕላን እንዲቆም ውሳኔ አሳለፈ። ማዕከላዊ ኮሚቴው ለሶስት ቀናት በአዳማ ተሰብስቦ ማስተር ፕላኑ እንዲቆም መወሰኑን በገለጸበት ማግስት ተቃውሞ የቀጠለ ሲሆን፣ ግድያም ቀጥሎ ዛሬ አምቦ ከተማ አንዲት ህጻን ስትገደል ሌላ ህጻን ቆስላለች። በድሬደዋና በአምቦ ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞ መቀጠሉ ተመልክቷል። በምዕራብ ሃረርጌ በቀጠለው ተቃውሞ ደግሞ 23 ተማሪዎች ተይዘው መታሰራቸው ይፋ ሆኗል።
በትንሹ በሁለት ወራት 150 ያህል ሰዎች ለተገደሉበትና በመቶዎች ለቆሰሉበት ድርጊት ቀጥተኛ መነሻ የሆነ ማስተር ፕላን ሙሉ በሙሉ መቆሙ ቢግለጽም፣ እቅዱ ስለመሰረዙ ግን የታወቀ ነገር የለም። የፖለቲካ ተንታኞች የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ እቅዱን የማቆም ስልጣን አለው ወይ በማለት የጠየቁ ሲሆን፣ ሰረዝኩት ከማለት ይልቅ አቆምን በሚል የተገለጸውን በጥርጣሬ ተመልክተውታል። አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የፖለቲካ ተንታኝ ለኢሳት “የማስተር ፕላኑን ትግበራ [ለጊዜው] ሙሉ በሙሉ አቆምን አሉ እንጂ፣ ሰረዝነው አላሉም፥ በመሆኑም ህወሃት ኢህአዴግ ባስፈለገው ጊዜ አንቀሳቅሶ ተግባራዊ ሊያደርገው ይችላል” ብለዋል።
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላትን ልዩ መብትም በቅርቡ ምላሽ እንደሚሰጠው ያመለከተ ሲሆን ግድያውን የፈጸሙትና የሃይል ጥቃቱን ባስከተሉት ወገኖች ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ ስለመኖሩ አልተጠቀሰም።
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫን ተከትሎ ጥያቄ አንስተው ተቃውሞ እያቀረቡ ያሉ አክቲቪስቶች ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ባልቀረቡበት ሁኔታ ውስጥ ተቃውሞ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዚህ በድሬደዋና በአዳማ ዩንቨርስቲ ረቡዕ በተከሰተው ተቃውሞ በተለይ በድሬዳዋ በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን ማንነቱን ማረጋገጥ ባይቻልም አንድ ተማሪ መገደሉ ተመልክቷል።
በአምቦ ከተማ ሰሞኑን በተገደለው አብደታ ኦላንሳ የቀብር ስነስርዓት ላይ በተገኙ ነዋሪዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ አንዲት ህጻን ስትገደል ሌላ ህጻን መቁሰሏ ፎቶግራፋቸው ተብትኗል። ሰሙዔል ተሰማ የተባለ የ11 አመት ወጣት ሰሞኑን በጥይት ተመትቶ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህክምና ላይ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን የልጁ አባት በዶ/ር መረራ ጉዲና የሚመራ ኦፌኮ አባል መሆናቸው ታውቋል።