በቀን ከ150 በላይ ኢትጵያዊያን ከአገራቸው ይሰደዳሉ ተባለ

ጥር ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከስደተኛ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ውስጥ አብዛሃኞቹ በእድሜ ወጣቶች ሲሆኑ፣ በጾታ ስብጥር ደግሞ በመቶኛ ሲሰላ 94 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ኮሚቴ በሂልተን ሆቴል ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ለፍልሰቱ ዋናው ምክንያት ሥራ አጥነትንና ሕገወጥ ደላሎችን በምክንያትነት አቅርቧል።
ወላጆች ተበድረው ለደላላ በመክፈል ልጆቻቸውን ወደ ውጭ ሀገራት እንደሚልኩ ኮሚቴው ቢገልፅም፣ ወጣቶችን ከአገራቸው እንዲሰደዱ ገፊ ኃይል የሆነውን ዋናውንና አንኳሩን የስርዓተ-ማኅበሩን ሙስና፣ዘረኝነት፣ የፖለቲካ ወገንተኝነት፣የትምህርት ስርዓት መበላሸት የመሳሰሉትን ምክንያቶች ጥናቱ አልዳሰሳቸውም።
ኢትዮጵያዊያን በጎረቤት አገራት ሶማሊያ፣ኬንያ፣ሱዳንና ጅቡቲ ጨምሮ ለሕይወታቸው አስጊ የሆኑትን በርሃዎችና ባሕሮችን እያቆራረጡ በአራቱም ማእዘናት መፍለሳቸውን ቀጥለዋል። በአፍሪካን ጨምሮ በአረብ አገራት እስር ቤቶች ውስጥ በርካታ ዜጎች በሰቆቃ ውስጥ እንዳሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይገልጻሉ።