የግቡፁ ፕሬዚዳንት ከመከላከያና ደህንነት ሃላፊዎች ጋር በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ መከሩ

ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008)

የግቡፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ከሃገራቸው የመከላከያና ደህንነት ሃላፊዎች ጋር በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ መምከራቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ማክሰኞ ዘገቡ።

ሰኞ በተካሄደው በዚሁ ዝግ ውይይት ፕሬዚደንቱ በቅርቡ ተደርሰዋል በተባሉ ስምምነቶችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በሰፊው መምከራቸውን አል-አህራም የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።

ፕሬዚደንቱ ከከፍተኛ የመከላከያና የደህንነት ሃላፊዎች ጋር ምክክርን አካሄደዋል ቢባልም ውይይቱ በዚህ ደራጃ ለምን እንደተካሄደና በምን አበይት ጉዳዮች ዙሪያ እንደመከረ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።

በዚሁ ልዩ የምክክር መድረክ የግብፁ የመስኖ ሚኒስትር ሆሳም ሞግሃዚ በመገኘት እየተካሄዱ ባሉ ድርድሮች ላይ ማብራሪያ ማቅረባቸውም ታውቋል።

የግብፅ ጋዜጠኞችን ያካተተ የሃገሪቱ ልዩ የልዑካን ቡድንም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ግድቡን እንደሚጎበኝ የፕሬዚደንቱ ጽ/ቤት አስታውቋል።

ሁለቱ ሃገራት በቅርቡ በሱዳን ባካሄዱት ድርድር የግድቡን ተጽዕኖ የሚያጠኑ ኩባንያዎች ስራቸው እስከሚያጠቃልሉበት ድረስ ግድቡን በውሃ የመሙላቱ ሂደት እንዳይካሄድ ውሳኔ መደረሱን የግብፅ ባለስልጣናት መግለጻቸው የታወሳል።

በካርቱም የተደረሰውን ስምምነት ተፈጻሚነት ለመከታተልም የኢትዮጵያና የግብፅ የባለሙያዎች ቡድን ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ ምክክር እያካሄደ ሲሆን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አዲስ የተደረሰ ስምምነት የለም በማለት ከግብፅ የተሰጠን ማብራሪያ አስተባብለዋል።

ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ለስምንት ወራት ጥናታቸውን የሚያካሄዱት ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች የሚያቀርቡት የጥናት ውጤት ያለ ይግባኝ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለግድቡ ግንባታ አለም አቀፍ ብድርንና ድጋፍን እንዳያገኝ ተፅዕኖ አሳድራለች የምትባለው ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ አለኝ የምትለውን ጥቅም ለማስጠበቅ የተቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።