ኢሳት (ጥር 3 ፥ 2008)
መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገ የኖርዌይ ኤምባሲ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዳግም በማገርሸቱ ምክንያት ዜጎች በክልሉ በሚያድርጉት ጉዞ ላይ የጥንቃቄ እርምጃን እንዲወስዱ አሳስቧል።
የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በቅርበት የምትከታተለው ኖርዌይ እየተካሄደ ያለው ተቃውሞ የጸጥታ ስጋት ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በቅርቡ ለኤምባሲ ተወካዮች በሰጡት ማብራሪያ ተቃውሞው በቁጥጥር ስር ዉሏል ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይሁንና በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደው ውይይት ተከትሎ ኖርዌይ ተቃውሞው አለመብረዱንና የጸጥታ ስጋት እየሆነ መምጣቱን በይፋ ስትገልጽ የመጀመሪያ ሃገር ሆናለች።
መቀመጫቸውን በሃገሪቱ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ተወካዮችና አለም አቀፍ ድርጅቶች በወቅታዊው የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ የተናጥል ምክክርን እያካሄዱ እንደሚገኝም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።