ኬንያ በኢትዮጵያ ድንበር ተጨማሪ ወታደሮችን አሰማራች

ኢሳት (ጥር 2 ፣ 2008)

በኢትዮጵያና የኬንያ ድንበር አካባቢ በሳምንቱ መገባደጃ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ኬንያ ተጨማሪ ወታደሮችን በድንብር ዙሪያ አሰማራች።

ከኢትዮጵያ የዘዘቁ ታጣቂዎች ቅዳሜ አንድ የኬንያ ተጠባባቂ ባልደርባን የገደሉ ሲሆን፣ በድርጊቱም በርካታ የቤት እንስሳትቶችም እንደተወሰዱ የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ከኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው ገብተዋል የተባሉ ታጣቂዎች በአንድ ተሽከርካሪ ላይ የተኩስ እርምጃ በመክፈት አብዲ ኤደን የተባለ የሃገሪቱ ተጠባባቂ ሃይል ባልደርባ መገደሉን የማርሳቤት ግዛት ፖሊስ ኮማንደር ማርክ-ዋንጀላ ለኬንያ ቴለቪዝን ኔትወርክ አስረድተዋል።

ከሳምንት በፊት በድንበር አካባቢ ተፈጽሞ በነበረ ተመሳሳይ ድርጊት ሁለት ኬንያዊያን በኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ታግተው መወሰዳቸውን ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ምርመራ ተካሄዶባቸው እንደነበር የተናገሩት ሁለቱ ኬንያውያን የፀጥታ ሃይሎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች ያሉበትን ስፍራ እንዲናገሩ ግፊት ተደርጎባቸው እንደነበርም ከተለቀቁ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

ቅዳሜ በተመሳሳይ አካባቢ የተፈጸመው ግድያም በሁለቱ ሃገራት ድንበር አካባቢ የጸጥታ ስጋት እንዲያይል ማድረጉን ነዋሪዎች አስታውቀዋል።

በኬንያ ተጠባባቂ ሃይል ባልደርባ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎም ኬንያ ተጨማሪ የጸጥታ ሃይሎችን በአካባቢው አሰማርታ እንደምትገኝ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሁለቱ ሃገራት ከወራት በፊት በድንበር አካባቢ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ ስምምነት ቢፈራረሙም የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች የሚወስዱት ድንበርን የመዝለቅ ድርጊት አለማብቃቱ ይነገራል።

የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ተፈላጊ የኦነግ ታጣቂዎችን ለመያዝ ነው በሚል ድርጊቱን እንደሚፈጽሙ የማርሳቤት ግዛት የፖሊስ ሃላፊ ኮማንደር ማር ዋንጀላ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ እስካሁን ድረስ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።