ኢሳት (ታህሳስ 27 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ከ180 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ወደአሳሳቢ ደረጃ እየተሸጋገረ መምጣቱንና ድርቁ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ፍጆታ በሶስት እጅ እጥፍ ማደጉን የአለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ገለጠ።
በተያዘው ወር ለተረጂዎች ከሚያስፈልገው የእርዳታ አቅርቦት ውስጥ ከአምስት በመቶ ብቻ የሚሆነው መገኘቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ሽቴፈን ዱጃሪክ አስታውቀዋል።
በወቅታዊው የኢትዮጵያ የድርቅ ሁኔታ ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጽ/ቤት መግለጫውን የሰጡት ሃላፊው በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለውን ይኸው የድርቅ አደጋ አለም አቀፍ ርብርብ የሚፈለግበትን ደረጃ መድረሱን ይፋ ማድረጋቸውን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በቀጣዮቹ ሶስት ወራቶች ውስጥም የተረጂዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችልና የእርዳታ አቅርቦቱ መሻሻልን ካላሳየን የከፋ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ሃላፊዎች አሳስበዋል።
ከተያዘው ወር ጀምሮ አስቸኳይ የምግብ እርዳታን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር 18 ሚሊዮን አካባቢ መድረሱን መንግስት ማክሰኞ ይፋ ያደረገ ሲሆን የአለም አቀፍ ማህበረሰብም በቂ ድጋፍን አለመለገሱ አስታውቋል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም የተረጂዎች ቁጥርና የእርዳታ አቅቦቱ ባለመጣጣሙ ምክንያት ችግሩ ኣየተባባሰ መምጣቱን ቢገልፅም መንግስት ለሶስት ወር የሚሆን የእህል ክምችት በሃገር ውስጥ መኖሩን ይገልጻል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት በበኩላቸው ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች በቂ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ምክንያት ከቀዬያቸው የሚፈናቀሉና ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ህጻናት እየጨመረ መምጣቱን ይፋ አድርጓል።
በተለይ በአደጋው ክፉኛ የተጎዱ የሶማሌ ክልል አካባቢ አርብቶ አደሮች ወደጎረቤት ጅቡቲና ሶማሊያ በመሰደድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡ ወደ አምስት ሚሊዮን ህጻናት መካከል ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደሚገኙና ወደግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናትም ለከፋ የምግብ እጥረት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት መረጃ አመልክቷል።
በስድስት ክልሎች በሚገኙ ከ 180 በላይ ወረዳዎች ውስጥ ጉዳትን እያደረሰ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ እስከቀጣዩ አመት መጋቢት ወር ድረስ ይዘልቃል ተብሏል።