ኢሳት (ታህሳስ 27, 2008)
ረቡዕ በአዲስ አበባ ምክክርን የጀመሩት የኢትዮጵያና የግብፅ የባለሙያዎች ቡድን የአባይ ግድብ የዲዛይን ማሻሻያ ሊደረግበት በሚችል ሁኔታ ላይ ኣንደሚወያዩ የግብፅ ባለስልጣናት ይፋ አደረጉ።
አምስት የባለሙያዎች ቡድንን ያካተተው የሃገሪቱ ልዑካን ለሁለት ቀን በሚቆየው ድርድር ላይ ይህንኑ ሃሳበ በማቅረብ ሰፊ ገለፃን እንደሚያደርግ የግብፅ የመስኖ ልማት ሚኒስትር ሆሳም ሞግሃዚ ለአል-አህራም ጋዜጣ ገልጸዋል።
ረቡዕ በአዲስ አበባ ስለጀመረው የሁለቱ ወገኖች ድርድር በተመለከተ ዝርዝር መረጃን ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት ሚኒስትሩ፣ የባለሙያዎቹ ተወካዮች የግብፅን ጥቅም ለማስጠበቅ የተለያዩ ሃሳቦችን ሲያጠኑ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።
በመገንባት ላይ ያለውን የአባይ ግድብ ለመጎብኘትም የግብፅና የሱዳን ፈቃድ መገኘት እንዳለበት በቅርቡ ስምምነት ላይ መደረሱን ሚኒስትሩ በድጋሚ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በሱዳን በተፈረመው ስምምነት አዲስ ሃሳብ የለም በማለት ቢያስተብሉም የግብፅ የመስኖ ልማት ሚኒስትር ግድቡን አስመልክቶ በርካታ ስምምነቶች መደረጋቸውንና ሃገራቸው ደስተኛ መሆኗን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ድርድርም ግብፅ በካርቱም የተደረሱ ስምምነቶች ተግባራዊ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ሚኒስትሩ ሆሳም ሞግሃዚ አስታውቀዋል።
የአባይ ግድብ በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለማጥናትም ሁለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ስራቸውን በቀጣዩ ወር የሚጀምሩ ሲሆን የኩባንያዎቹ ውጤትም ይግባኝ በሌለው ሁኔታ ተፈፃሚ የሚሆን እንደሚሆን ተነግሯል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለውን ድርድር በተመለከተ ከኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ድረስ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።