ድርቁ እየተባባሰ በመጣባቸው አካባቢዎች የትምህርት ሰራው እየተጎዳ መምጣቱ ተነገረ፡፡

ታኀሳስ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሰሜን ጎንደር ዞን በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች በተከሰተው ድርቅ ፣ የሚያስተምሩ መምህራን በየጊዜው ስራቸውን በመልቀቃቸው የትምህርቱ ስራ አደጋ ላይ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ከፍተኛ ባለስልጣናት በጎንደር ከተማ በሰጡት መግለጫ ተናገሩ፡፡
በዞኑ ባሉት 280 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ከ120 ሽህ በላይ ህጻናት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቆም በቋፍ ላይ መሆናቸወን የተናገሩት የዞኑ አመራሮች በተለይ በወገራ፣ምስራቅ በለሳና ጃናሞራ ወረዳዎች በሁለት ሳምንት ብቻ 265 መምህራን መልቀቃቸውን ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
በጃናሞራ ወረዳ አሁን አሁን የመበተን አዝማሚያ እየታየ መሆኑን የዞኑ የትምህርት ከፍተኛ ኃላፊዎች ገልጸው፤ሰፊ የደርቅ አደጋ በታየባቸው 120 ቀበሌዎች የትምህርቱ ሂደት አደጋ ላይ መውደቁን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ያለውን የትምህርት ሂደት ለማስቀጠል የመምህራን መልቀቅ መሰረታዊ ችግር መሆኑን የሚናገሩት አመራሮች አሁንም የተሰጠ አስቸኳይ መፍትሄ ባለመኖሩ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከድህነቱ ጋር ተያይዞ ከባድ የጽህፈት መሳሪያ እጥረት ችግር መኖሩ አንዱ የመማር ማስተማሩን ሂደት አደጋ ላይ የሚጥል ችግር መሆኑን አክለው የሚናገሩት የትምህርት አመራሮች፣ አንድ ደብተር ለአራትና አምስት ተማሪዎች የሚጠቀሙበትን ሁኔታ በአካል በመገኘት መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርቁ በተከሰተባቸው ሰባቱም ወረዳዎች ለህጻናቱ አስቸኳይ አልሚ ምግብ ካልቀረበላቸው የሞት አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ስጋቱ እንዳደረባቸው የሚገልጹት ኃላፊ ከረሃቡ ጋር በተጨማሪ የውሃ እጥረቱም ለተማሪዎች ፈታኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአንድም ይሁን በሌላ ችግር የመቅረትን ሁኔታ እያባባሰው ያለው የተከሰተው የውሃ ችግር መሆኑን የሚገልጹት ኃላፊ አንድ ጀሪካን ውሃ ለማምጣት ህጻናቱ የስድስት ሰዓት መንገድ የሚጓዙ በመሆኑ የቀሪ ተማሪዎች ብዛት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱ በትምህርቱ ላይ ያንዣበበ ትልቅ አደጋ መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
በሰሜን ጎንድር ድርቁ በተከሰተባቸው ሰባት ወረዳዎች 245 ሽህ ህዝብ ለችግር የተጋለጠ ሲሆን በተለይ ምስራቅ በለሳ-ሰባት፣ወገራ-ስምንት፣ደባርቅ-ሶስት፣ጃናሞራ-ዘጠኝ እና ጠለምት-ሰባት ቀበሌዎች ከፍተኛ የውሃ እጥረት ተከስቶባቸዋል፡፡ የገዥው መንግስት ቃል ከመግባት ባሻገር እስካሁን መሬት የነካ ስራ ለመስራት ባለመቻሉ አብዛኛው የአካባቢው ወጣቶች ወደ ጠረፍ ከተሞች በመሰደድ ነፍሳቸውን ለማቆየት ጥረት ሰያደርጉ ሴቶችና ህጻናትም በጎንደርና አቅራቢያ ባሉ ከተሞች ህጻናት ልጆቻቸውን በመያዝ በልመና ላይ መሆናቸውን ስፍራውን የለቀቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡