ኢሳት (ታህሳስ 23 ፣ 2008)
በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር በየአመቱ ከፍተኛ ገንዘብ የምታወጣው ኢትዮጵያ ከህገ-ወጥ ንግድ ተቋማት ጋር በተያያዘ በየአመቱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እያጣች እንደሆነ አንድ አለም አቀፍ የፋይናንስ ደህንነት ተቋም ይፋ አደረገ።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2004-2013 26 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ያጣችው ኢትዮጵያ ከዚሁ ገንዘብ መካከል 19.7 ቢሊዮን ዶላር ከህገወጥ ንግድ ጋር የተያያዘ መሆኑን ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተለጀንስ አስታውቋል።
ሃገሪቷ ከህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተገናኘ እያጣች ያለችው ገንዘብ ከሃገሪቱ አመታዊ አጠቃላይ ምርት ውስጥ ከ5-10 በመቶ የሚሆነውን እንደሚሸፍንና መጠኑም ከአህጉሪቱ ሰፊ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል።
ኢትዮጵያ በተጨማሪ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሜክሲኮ፣ ህንድ እና ማሌዥያ ከፍተና ገንዘብን በህገወጥ ዝውውር ከሚያጡ ሃገራት መካከል ዋንኞቹ መሆናቸውን የፋይናንስ ተቋሙ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ካላት አነስተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የውጭ ንግድ ገቢ አኳያም በየአመቱ እያጣች ያለው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የድርጅቱን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ዘ-ሲቲዝን የተሰኘ ጋዜጣ አርብ እለት ዘግቧል።
የአለም ባንክን ጨምሮ የብሪታኒያ መንግስትና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የምታጣውን ገንዘብ እንዲቀንስ ለማድረግ የስልጠናና የምክር ድጋፍን እየሰጡ ኣንደሚገኝም ታዉቋል።
በህገወጥ መንገድ ከሃገር የሚወጣው ገንዘብ በላኪና በአስመጪዎች እንዲሁም በሌሎች የገንዘብ ዝውውሮች መሆኑን የፋይናንስ የደህንነት ተቋሙ መረጃ አመልክቷል።
ሀገሪቱ እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2004 እስከ 2013 ድረስ ከሃገሯ የወጣው ወደ 26 ቢሊዮን ዶላርም በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ትግሉ ከ10 ዓመት በኋላም እልባት አለማግኘቱ ተገልጿል።
የመንግስት ባለስልጣናትም በበኩላቸው የህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ሲሉ ምላሽ መስጠት ዘሲቲዝን ጋዜጣ በዘገባው አስነብቧል።