በዲላ ዩንቨርስቲ ቦምብ ፈንድቶ 2 ተማሪዎች ሲሞቱ በርካታዎች ቆሰሉ

ኢሳት (ታህሳስ 23 ፣ 2008)

ሐሙስ ምሽት በዲላ ዩንቨርስቲ በደረሰ የእጅ ቦንብ ፍንዳታ ሁለት ተማሪዎች የሞቱ ሲሆን፣ በርካታ ተማሪዎችም ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ እንደሚገኙ ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተለያዩ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ላይ እየወሰዱ ያለው የእስር ዘመቻና ግድያ ተቃውሞው በድጋሚ እንዲቀሰቀስ ማድረጉን ለመርዳት ተችሏል።

ግድያ ይቁም የሚል መፈክሮችን በማሰማት ላይ የሚገኙት እነዚሁ ተማሪዎች የፅጥታ ሃይሎች ከትምህርት ተቋማት እንዲርቁ ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።

በዲላ ዩንቨርስቲ የደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ ተከትሎም በዩኒቨርስቲው የትምህርት ማስተማር ሄደቱ የተቋረጠ ሲሆን የእጅ ቦንብ አደጋው በምን ምክንያት ሊደርስ እንደቻለ የታወቀ ነገር የለም።

ሐሙስ በተለያዩ የምዕራብና ምስራቅ ወለጋ አካባቢ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችም አርብ መቀጠላቸውንና በከፍተኛ ተምህርት ተቋማት ዘንድ ውጥረት መከሰቱን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

መንግስት በበኩሉ በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል ባላቸው አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በድጋሚ ገልጿል።

መንግስት በበኩሉ በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል ባላቸው አካላት ላይ የሚወሰደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በድጋሚ ገልጿል።

ይሁንና እየተወሰደ ያለው የእስር ዘመጃ ከበርካት ተማሪዎች ዘንድ ሌላ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ማድረጉን የተለያዩ አካላት በማስታወቅ ላይ ናቸው።

ያገረሸውን ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ሃይል በከፍተኛ ትምህርት ትቋማት አካባቢ መሰማራቱ ታውቋል።

በእስካሁኑ የእስር ዘመቻም ወደ 5 ሺ የሚጠጉ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሰሞኑን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን አሜሪካና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የመንግስት እርምጃ አሳስቧቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለአንድ ወር ያህል ጊዜ በዘለቀው ተቃውሞ የሟቾች ቁጥር ከ 100 በላይ መድረሱ ይነገራል።