የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት አባላት ማህበር አባላቱ ከህዝቡ ጎን በመሆን እንዲታገሉ ጥሪ አቀረቡ

ኢሳት (ታህሳስ ፣ 2008)

የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አርበኞች ማህበር በኦሮሚያ ክልል በፀጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን ድርጊት በማውገዝ የቀድሞ የሰራዊት አባላት ህዝቡ እያካሄደ ካለው ትግል ጎን እንዲሰልፍ ጥሪን አቀረበ።

በስልጣን ላይ ያለው ገዢው የኢህአዴግ መንግስት መብታቸውን በሚጠይቁ ሰዎች ላይ የሚወስደው የግፍ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ማህበሩ፣ ህዝቡ ለሰላም ያለውን ተስፋም ጨልሞ እንደሚገኝ አስታውቋል።

እያንዳንዱ የቀድሞ ሰራዊት አባላት በያለህበት ሆነህ በመደራጀትና በመቀናጀት እንዲሁም እርስ በእርስ በመናበብ የኢትዮጵያ ህዝብ እያካሄደ ካለው ትግል ጎን እንዲሰለፍ ሲል ማህበሩ ጥሪውን አቅርቧል።

መቀመጫው በዚህ በአሜሪካ ያደረገው ይኸው ማህበር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ልዩነቱን በማስወገድና በመቻቻል የተጀመረውን ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥልም ሃሙስ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

በስልጣን ላይ ያለው ገዢው ኢህአዴግ መንግስት የሃገሪቱን መሬት አሳልፎ ለመስጠት ከሱዳን ጋር ያደረገው ድንበር የማካለል ስምምነት የሃገሪቱን ጥቅም የሚጎዳና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አርበኞች ማህበር አክሎ ገልጿል።

“የአገራችን መሬት ሲቆረስና ህዝባችን ሲጎዳም እጆቻችንን አጣምረን አንቀመጥም” ሲል የማህበሩ መግለጫ አመክቷል።