የህንዱ ኩባንያ ካራቱሪ ከመንግስት ጋር የነበረው ውል ተቋርጧል ተባለ

ኢሳት (ታህሳስ 21 ፣ 2008)

በጋንቤላ ክልል 100ሺ ሄክታር መሬትን በርካሽ ዋጋ ለ 50 ዓመታት ተረክቦ የነበረው የህንዱ ካራቱሪ ኩባንያ ከመንግስት ጋር የነበረው ውል ተቋረጠ።

ድርጅቱ ከመንግስት የተሰጠውን ወደ 60 ሚሊዮን ብር ብድርም መክፈል ሳይችል የቀረ ሲሆን፣ ከተረከበው 100ሺ ሄክታር መሬት ውስጥ ባልፉት ስድስት አመታት 1ሺ 200 ሄክታር መሬት ብቻ ማልማቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ የህንዱ ኩባንያ ሲያካሄድ የነበረው የስራ አፈጻጸም በጣም ዝቅተኛና ከተጠበቀው በታች በመሆኑ ዉሉ እንዲቋረጥ መደረጉን ሃሙስ ይፋ አድጓል።

ኩባንያው በእስካሁኑ ሂደት ያለማው መሬትም እንደሚነጠቅ የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ዳንኤል ዘነበ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ለህንዱ ኩባንያ ወደ 60 ሚሊዮን ብር በብድር ሰጥቶ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ የድርጅቱን መሬት በሃራጅ ለመሸጥ ጨረታን ቢያወጣም ኩባንያው ያቀረበውን አቤቱታ ተከትሎ ጨረታው እንዲታገድ ተደርጓል።

ከመንግስት በርካታ ድጋፎች ሲደረግለት የቆየው ኩባንያ የተረከበውን መሬት ለሶስተኛ ወገን ለማስተላለፍ ፍላጎት እንዳለው ለፍርድ ቤት አስረድቷል።

ይሁንና ካራቱሪ ኩባንያ መሬቱን የመሸጥ መብት የሌለው በመሆኑ ማድረግ የሚችለው መሬቱን የመጠቀም መብትን ማስተላለፍ እንደሆነ የህግ ባለሙያዎች አስረድተዋል።

ፍርድ ቤት ኩባንያውን ላቀረበው አቤቱታ የሚሰጠውን ውሳኔ ተከትሎም በባንኩና በህንድ ኩባንያ መካከል ድርድር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በጋንቤላ ክልል ተካሄዷል በተባለ የመሬት ቅርምት 100ሺ ሄክታር መሬትን በርካሽ ዋጋ የተረከበውና በመንግስት ብድር ስራውን ሲያካሄድ የነበረው ካራቱሪ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኪሳራን እንዳመጣም የባንክ ባለሙያዎች ገልጸዋል።