በኦሮሚያ ክልል ሰዎች በገፍ እየታሰሩ ነው፣ አቶ በቀለ ነገአ እንደተደበደቡ ገለጹ

ኢሳት (ታህሳስ 21 ፣ 2008)

በበርካታ የኦሮሚያ የክልል ከተሞች ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች እየታሰሩ እንደሆነ ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ አመራሮች ላይ እየተካሄደ ባለው በዚሁ ዘመቻ ከ4ሺ የሚበልጡ አባላት ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል። ይሁንና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን የእስር ዘመቻ በመቀጠሉ ቁጥሩ በየእለቱ እየጨመረ መምጣቱንና ትክክለኛ ቁጥሩን በአንድ ጊዜ መግለጽ አስቸጋሪ ኣየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።

የፓርቲው አመራሮች በአሁኑ ሰዓት በደህንነት ሃይሎች ክትትልና ዛቻ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል። የመንግስት ባለስልጣናት ከተቃውሞ ጋር ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ አድርገዋል ባሏቸው አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸው ተከትሎ በተለያዩ ከተሞች የቤት ለቤት ፍተሻ እየተካሄደ እንደሚገኝም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ፖሊስ በበኩሉ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራን እያካሄድኩ ነው ቢልም በቁጥጥር ስር ሰለዋሉ ሰዎች ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ከዚሁ ከኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ዋና ጸሃፊ አቶ በቀለ ነጋኣ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡና ለመገናኛ ብዙሃን ምንም አይነት ነገር እንዳይናገሩ እገዳ እንደተጣለባቸው ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ሃሙስ በፅጥታ ሃይሎች ታፍነው በተሽከርካሪ ከተወሰዱ በኋላ በቁም እስር ላይ የሚገኙት አቶ በቀለ በፅጥታ ሃይሎች እንግልትና ወከባ እንደተፈጸመባቸው ታውቋል።

በደህንነት ሃይሎች ድብደባ የተፈጸመባቸው የፓርቲው ዋና ጸሃፊ የተሰጣቸው ማሳሰቢያ ተግባራዊ ካላደረጉ የግድያ እርምጃ እንደሚፈጸምባቸው ጥብቅ ማሳሰቢያ እንደተሸጣቸውም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

አቶ በቀለ ነጋኣ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን ግድያና እስራት በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መረጃን ሲሰጡ መቆየታቸው ይታወሳል።

የኦፌኮ አመራሮችን ጨምሮ ከ4ሺ የሚበልጡ አባላትና ደጋፊዎች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኝ ከፓርቲው የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞው በቁጥጥር ስር ዉሏል ቢሉም በምዕራብ ሸዋ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተቃውሞ መቀጠሉ ታውቋል።