በተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች ለሳምንታት ሲካሄድ የሰነበተው ተቃውሞ ዛሬም ቀጥሎአል። በተለይ በምእራብ ሃረርጌዋ መቻራ ከተማ ህዝብ ነቅሎ በመውጣት ተቃውሞውን ሲያሰማ በሆድሮ ጉድሩ ደግሞ የተማሪዎችን ሰላማዊ ተቃውሞ ሌላ አቅጣጫ ለመስጠት በአካባቢው የተሰማሩት ወታደሮች በትምህርት ቤት ላይ ቦንብ ወርውረው አንድ ተማሪ መግደላቸውን የአሮሞ ፌደራሊስ ንቅናቄ ከፍተኛ አመራርና የቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ገብሩ ገብረማርያም ለኢሳት ተናግረዋል።
አቶ ገብሩ በክልሎ የሚካሄደው ተቃውሞ መንግስት እንደሚያስወራው ሳይሆን ተጠናክሮ መቀጠሉን በእየለቱ ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል። “ተቃውሞውን ማስቆም አይቻልም” ያሉት አቶ ገብሩ፣ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት መውጫ ሳያዘጋጁ ችግር እንዳይገጥማቸው ከተቃዋሚ መሪዎች ጋር ተነጋግረው ችግሩን እንዲፈቱ አሳስበዋል።
መንግስት ተቃውሞውን ይመራሉ ወይም ያበረታታሉ ያላቸውን እንደ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው፣ አቶ ዮናታን ተስፋዬና ሌሎችም ወጣት የዲሞክራሲ አቀንቃኞችን ቢያስርም ተቃውሞ ግን ሊቆም አልቻለም። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ በቀለ ነጋ በደህንነቶች ተይዘው መደብደባቸውን በፌስ ቡክ በለቀቁት ጽሁፍ ገልጸዋል።
“ዛሬ ጠዋት ወደ ስራ በምሄድበት ወቀት 4 የሲቪል ልብስ የለበሱ ሰዎች ስሜን ጠርተው ሰላም ካሉኝ በሁዋላ ፣ ፖሊሶች መሆናቸውን በመግለጽ መኪና ውስጥ እንድገባ ” ጠየቁኝ ያሉት አቶ በቀለ፣ አልገባም ስላቸው ሁለት እጆቼን ይዘው እየገፈተሩ ከሁዋላ ወንበር ላይ አስቀምጠውኝ መኪናውን አስነስተው ሄዱ ” ይላሉ።
መኪና ውስጥ በግራና በቀኝ የተቀመጡ ፖሊሶች መምታት መጀመራቸውን የገለጹት አቶ በቀለ፣ ፊት የተቀመጠው አንደኛው ፖሊስ በጠመንጃው ፊታቸውን እየነካ ሊያስፈራራቸው ሞክሯል።
“የምንደበድብህ ማስጠንቀቂያችንን ባለመስማት ለሚዲያ ስለምትናገር ነው” እንዳሉዋቸው የገለጹት አቶ በቀለ፣ መደብደባቸውን ሲያቆሙ ሞባይል ስልኬን ነጥቀው ከወሰዱ በሁዋላ፣ ትእዛዛቸውን የማልፈጽም ከሆነ የእኔ ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቼ ህይወትም አደጋ ላይ መውደቁን ፣ ” ከዛሬ ጀምሮ ከቤትህ ብትወጣ ወይ ለሚዲያ ብትናገር በአንተም ሆነ በቤተሰቦችህ ላይ ለሚሆነው ሃላፊነቱ ያንተ ነው” እንዳሉዋቸው ገልጸዋል።
ከመልቀቃቸው በፊት ” ከእንግዲህ ወዲህ አንተን የምናስርበት ቦታ የለንም፣ ወይ እንገድልሃለን ወይ በመኪና ገጭተን ፓራላይዝ እናደርግሃለን” እንዳሉዋቸው አቶ በቀለ ጽፈዋል።
መንግስት በኦሮምያ የሚያደርሰውን ጭፍጨፋ እንዲያቆም ቢጠየቅም ፈቃደኛ አልሆነም ያሉት አቶ በቀለ፣ የድርጅታቸው አባላት የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላና ደስታ ዲንቃ ከሰው እንዳይገናኙ ተደርገው መታሰራቸውን አውስተዋል።
መንግስት ንጹሃን ዜጎችን በመግደል ወይም በማሰር ተቃውሞውን ዝም ለማሳኘት እንደማይችል የገለጹት አቶ በቀለ፣ እኔና ሌሎች የፓርቲው አባሎች ሰላማዊ ትግሉን በመቀጠል የህይወት መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።
ኢሳት አቶ በቀለን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያድርግም ስልካቸው በመዘጋቱ ሊሳካለት አልቻለም።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢሳትና ኦኤምን ታያላችሁ በሚል 15 አርሶአደሮች በቦረና ዞን ዱቅሳ መጋላ ቀበሌ ተይዘው ወደ መገዳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተወስደው እየተደበደቡ መሆኑንና እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።