ኢሳት (ታህሳስ 19 ፣ 2008)
በቅርቡ ግንባር የፈጠሩት የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ጥምረት እና የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ንቅናቄ የጀመሩትን ትግል በቁርጠኝነት ለማካሄድ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር በመሆን የጋራ የትግል ስምምነቶን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ወሰኑ።
የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ጥምረት ግንባርን የመሰረቱት ድርጅቶቹ የተጀመረውን ትግል ለማጠናከርና ከግብ ለማድረስ በጋራ መስራትን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
“የጋራ ትግላችን ፈርጀ ሰፊና፣ ሁሉን አቀፍ ነው” ሲል የገለጸው ጥምረቱ፣ ገዢው የኢህአዴግ መንግስት በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ በርካታ ከተሞች የፈጸሙውን ግድያ በማውገዝ ከኦሮሞ ህዝብ ጎን እንደሚቆም ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በመንግስት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የመሬት ቅርምት እርምጃም፣ በርካታ ሰዎችን ለጎዳና ተዳዳሪነትና ለስደት ዳርጎ እንደሚገኝ ጥምረቱ አስታውቋል።
በዚሁ ችግር የተነሳ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሰው ሃገር ችግር እየደረሰባቸው እንደሆነ የገለጸው የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ጥምረት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጀመረውን ህዝባዊ ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል።
ገዢው መንግስት በቅርቡ ከሱዳን ጋር ድንበር ለማካለል የደረገው ስምምነትም ተቀባይነት የሌለውና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ እንደሆነ ጥምረቱ አክሎ አስታውቋል።