ታኀሳስ ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሱዳን፣ ግብጽና ኢትዮጵያ መካከል ካርቱም ላይ የተፈረመው ስምምነት የግብጽ ባለስልጣናትን ማስደሰቱን የተለያዩ የግብጽ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።
አህራም ኦን ላይን የግብጽ የመስኖ ሚኒስትርን ጠቅሶ እንደዘገበው ስምምነቱ የግድቡን አጠቃላይ አሰራር የሚገመግሙት ሁለቱ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ውሳኔ እስከሚሰጡ ድረስ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የምታደርገውን ግንባታ እንድታቋርጥ እንዲሁም በግድቡ ውሃ ለመሙላት እንደማትችል በወረቅት ላይ ስምምነቷን መግለጿን ተናግረዋል።
ሚኒስትር ሆሳም ሞጋዚ እንዳሉት ኢትዮጵያ የግብጽና የሱዳን ባለስልጣናትና የውሃ አጥኚዎች ግድቡን እንዲጎበኙ ተስማምታለች። ቀድም ብሎ ጥናት እንዲያካሂድ ተመርጦ የነበረው የሆላንዱ ዴልታሬስ ኩባንያ ነጻና ገለልተኛ ጥናት ለማድረግ አይቻልም በሚል ራሱን በማግለሉ የፈረንሳዩ አርቴሪላ ኩባንያ ከቢአር ኤል ኩባንያ ጋር በጋራ እንዲሰራ መመረጡን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አዲሱን ስምምነት በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል ግልጽ የሆነ መረጃ አልተሰጠም። ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ግድቡን የማጠናቀቅ ብቃት ቢኖራት እንኳን ከ8 እስከ 12 ወራት ባሉት ጊዜያት ግድቡን ውሃ የመሙላት መብት የላትም። የግድቡ እጣ ፋንታ በፈረንሳይ አጥኚ ኩባንያዎች ላይ የሚወድቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ይዛው ከነበረችው አቋም መለሳለሱዋ የግብጽ ባለስልጣናትን አስደስቷል። የግብጽ ሚዲያዎች ሰሞኑን ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ የመሙላት ስራ ልትጀምር ነው በማለት ተደጋጋሚ ዘገባዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።