ኢሳት (ታህሳስ 19 ፣ 2008)
በኢትዮጵያ አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የድርቅ አደጋ ተከትሎ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ልዩ የምግብ ድጋፍና የቅርብ ክትትልን የሚፈልጉ ህጻናትና ነፍሰጡር እናቶች ቁጥር ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ መድረሱን የተባበሩት መግስታት ድርጅት ይፋ አደረገ።
እነዚህ ተረጂዎች አስፈላጊው ድጋፍ ካልቀረበላቸውም የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሚሆን ድርጅቱ አሳስቧል።
ልዩ የምግብ ድጋፍና የጤና ክትትልን የሚፈልጉ ህጻናትና እናቶችን ቁጥር በቅርቡ ወደአንድ ሚሊዮን አካባቢ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ይህ ቁጥር በቅርቡ ወደሁለት ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መግስታት ድርጅት አስታውቋል።
እነዚሁ ተረጂዎችም በአፋር፣ አምሃራ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ ደቡብና ትግራይ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅርትም ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች በቂ የምግብ ድጋፍ እየቀረበ አለመሆኑን ድርጅቱ ባወጣው ሪፖርት አክሎ አመልክቷል።
ይኸው ከ180 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ውስጥ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋ ከምግብ እጥረት በተጨማሪ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩንም የአለም ጤና ድርጅት በድጋሚ አሳስቧል።
ሀገሪቱ ችግሩን የመቋቋም አቅም የሌላት በመሆኑ ድጋፍ የሚሰጥ አለም አቀፍ የህክምና ቡድን አባላት በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ተሰማርተው እንደሚገኙ ድርጅቱ ገልጿል።
ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚቀርበው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ተከትሎም ለተረጂው የሚሰጠው የእርዳታ መጠን እንዲቀንስ መደረጉን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ተረጂዎች እርዳታን በየሁለት ሳምንት ሳይሆን በወር አንድ ጊዜ እንዲያገኙ መደረጉን የተባባሩት መንግስታት ድርጅት ድርጅት አስታውቋል።
ከአስር ሚሊዮን በላይ የደረሰው የተረጂዎች ቁጥርም በጥቂት ወራቶች ውስጥ ወደ 15 ሚሊዮን ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል።