ኢሳት (ታህሳት 19 ፣ 2008)
ላለፉት ሶስት ቀናቶች በሱዳን ካርቱም 11ኛ ዙር ድርድራቸውን በአባይ ግድብ ዙሪያ ሲያካሄዱ የሰነበቱት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና፣ ሱዳን ባለፈው አመት በመሪዎች በመርህ ደረጃ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ማክሰኞ ገለጡ።
ከግድቡ ጥናት ራሱን ባገለለው የኔዘርላንዱ ኩባንያ ምትክም፣ ሌላ ድርጅትን በመምረጥ ጥናቱ በአስቸኳይ እንዲካሄድ መወሰናቸውን ሺንሃኣ ዘግቧል።
ባለፈው አመት የካቲት ወር ላይ የሶስቱ ሃገራት መሪዎች ታሪካዊ ነው የተባለለትን ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ ስምምነት ሶስቱ ሃገራት ወንዙ በፍትሃዊነት ለመጠቀም መወሰናቸው ተገልጿል።
የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሄም ጋንዱር በካርቱም የተደረሰውን ስምምነት በሶስቱ ሃገራት አለመግባባት መንስኤ ሆነው የቆዩ ጉዳዮችን የሚቀርፍ እንደሆነ ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ሶስቱ ሃገራት የደረሱበት ስምምነት ታሪካዊ ነው ቢሉም፣ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መግለጫን ሳይሰጡ ቀርተዋል።
የግብፅ ባለስልጣናት በበኩላቸው ስምምነቱ ወሳኝ ቢሆንም፣ በግድቡ ላይ የሚካሄደው የጥናት ውጤት ወሳኝ መሆኑን ለመግለጽ ለግብፅ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በሶስት ሃገራት መተማመን እንዲኖር ያስችላል የተባለው የካርቱሙ ስምምነት ተከታታይ ውይይቶች እየተካሄዱበት የሚሻሻል መሆኑንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስታውቀዋል።
በመለስተኛው የሶስትዮሽ ስምምነት ሃገራቸው ደስተኛ መሆኗን የተናገሩት የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳምህ ሹክር በበኩላቸው ወደ ተሻለ ምዕራችፍ ተሸጋግረናል ሲሉ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም እንዲሁ በሶስት ሃገራት መካከል የሚፈረመው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ጠቃሚ እንደሆነና ሃገራቸው ለግንኙነቱ ስኬታማነት እንደምትሰራ ከስምምነቱ በኋላ መግለጻቸውን ሺንሃኣ ዘግቧል።
አል አህራም የተሰኘ የግብፅ ጋዜጣ በበኩሉ፣ ሶስቱ ሃገራት በተደጋጋሚ ስምምነትን ኣንዲደርሱ ቢገልፁም አሁንም ድረስ ወደአለመግባባት የሚወስዱ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ አስነብቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ሶስቱ ሃገራት ማክሰኞ በፈረሙት ስምምነት ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ መሙላት በምትጀምርበት ጊዜ የታችኞቹ ተፋሰስ ሃገራትን ጥቅም ለመጠበቅ የሚያስች አንቀጽ መኖሩን ሮይተርስ ዘግቧል። ይሁንና ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ የመሙላትና ሂደት ያለግብፅ ፈቃድ በምንም መልኩ እንደማታካሄድ መፈረሟ ታውቋል።