ታኀሳስ ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የባንኩ ሰራተኞች እንደገለጹት ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዲዋሃድ የተደረገው ከጀርባው ያለውን የዘረፋ ወንጀል ሽፋን ለመስጠት ነው።ሰራተኞቹ በዘረፋው ወንጀል የበላይ የመንግስት አካላት እንዳሉበት ይገልጻሉ።
ባንኩ በ2008 ዓም 12 ሚሊዮን ብር መክሰሩን የሚገልጹት ሰራተኞች ለኪሳራው ምክንያት ናቸው ያሉዋቸውን በርካታ የሙስና ወንጀሎች ዘርዝረው አቅርበዋል።
ባንኩ አገልግሎትን እንዲያቀላጥፍ በሚል ቲ 24 የተባለ Core Banking software ቢገዛም ፣ ለግዢው የወጣው ወጪ ግን በአገሪቱ የሚገኙ ሌሎች የግል ባንኮች ካወጡት በሶስት እጅ ይልቃል። አብዛኞቹ የግል ባንኮች 80 ሚሊዮን ብር አውጥተው ሶፍትዌሩን የገዙ ሲሆን፣ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ግን ለተመሳሳይ ምርት 300 ሚሊዮን ወጪ አድርጓል። ባንኩ በድንገት ከንግድ ባንክ ጋር እንዲዋሃድ መደረጉ ንግድ ባንክም ተመሳሳይ ሶፍትዌር ያለው በመሆኑ ለዚሁ ግዢ ተብሎ የወጣው 300 ሚሊዮን ብር ዋጋ አልባ የሚያደርገው ነው ሲሉ ሰራተኞች ይገልጻሉ።
እንዲሁም ይላሉ ሰራተኞች 20 የአውቶማቲክ ቲለር ማሽን (ATM) ለመግዛት 20 ሚሊዮን ብር ወጪ ቢደረግም፣ ማሽኖቹ ጊዜ ያለፈባቸውና የአገለገሉ በመሆናቸው ከተገዙበት ከ4 አመታት ጀምሮ እስከዛሬ ሊሰሩ ባለመቻላቸው እንዳይታዩ በሚል በመጋዝን ውስጥ ተቀምጠዋል።
በቅርቡ በግብር ማጭበርበር ተከሶ ባለቤቶቹ ለእስር የተዳረጉት ትህዳር ኮንስትራክሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በባንኩ ፕሬዚዳንት ትእዛዝ 28 ሚሊዮን ብር ብድር የተፈቀደላቸው ሲሆን፣ ይሁን እንጅ ድርጅቱ የታገደና ንበረቶቹም የታገዱ በመሆኑ የባንኩ ብድር ወደ ተበላሸ ብድር እንዲዛወር መደረጉን ሰራተኞች ገልጸዋል።
የአሁኑ ም/ል ጠ/ሚኒስትር እና የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን እንጅባራ በምትባል ከተማ ለሚሰሩ 2 ሆቴሎች ለእያንዳንዳቸው 15 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲሰጥ በማዘዛቸው ፣ ባለሀብቶቹ በአንድ አመት ግንባታውን ማጠናቀቅ የሚገባቸው ቢሆንም፣ በ3 አመታት ለማጠናቀቅ ባለመቻላቸው እና ክፍያ ባለመጀመራቸው ወደ ተበላሸ ብድር መዞር ሲገባቸው የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጡ ጤናማ ብድር ሆነው እንዲቆዩ መደረጉን ሰራተኞች ይገልጻሉ።
እንዲሁም በባንኩ ፕሬዝዳንት ልዩ ትእዛዝ ከባንኩ መመሪያና ደንብ ውጪ ቦሌ ስካይ ለተባለ ሆቴል ያለ ባለቤቱ የድርሻ መዋጮ መቶ በመቶ ከባንኩ ብድር እንዲሰጠው የተደረገ ሲሆን፣ ተበዳሪው በየወሩ መክፈል የሚገባውን የብድር ክፍያ መፈፀም ያልቻለ ቢሆንም የጊዜ ማራዘሚያ እየተሰጠው እንደሚገኝ ሰራተኞች ይናገራሉ።
ለባንኩ ያለው ጠቀሜታ በጥናት ሳይረጋገጥ ERP ሶፍትዌር በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር አውጥቶ ለመግዛት ቅድሚያ ክፍያ 20 ሚሊዮን ብር መከፈሉ በተለይ ተመሳሳይ ግዢ እየፈፀመ ካለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እንዲዋሀድ መወሰኑ፣ በግዢው ሰበብ የሚገኝ የግል ኮሚሽን ከማሰብ በቀር ሌላ ፋይዳ የለውም ሲሉ ሰራተኞች ያስረዳሉ።
የባንኩ የንብረት አስተዳደር ዳሬክተር፤ የግዢ ሀላፊ፤ የውስጥ ቁጥጥር ዲሬክተርና የፋይናንስ አስተዳደር ዲሬክተር እና የብድር ግንኙነት ማናጀር የነበሩት ሃላፊዎች በፈቃዳቸው ስራቸውን ለቀው የወጡ ሲሆን ሊሎች የበታች ሰራተኞችም በቅጣትና በዝውውር ስም ወደተለያየ የስራ መደብ በመዛወራቸው ጉዳዩን ለማድበስበስ እየተሞከረ እንደሚገኝም ሰራተኞች ተናግረዋል።
ባንኩ በተለያዩ ወንጀሎች ምክንያት ለኪሳራ የተዳረገና በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያው የከሰረ ባንክ ለመሆን በቅቶዋል የሚሉት ሰራተኞች፣ ከላይ የተፈፀሙት ወንጀሎች በፀረ ሙስና ኮሚሽን እየተጣሩ ቢሆንም በአንዳንድ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጉዳዩን ለማዳፈን ሽፋን እየተሰጠና እያከላከሉ ይገኛሉ ብለዋል።
በሌላ በኩል የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ለህይወት እርሻ ሜካናይዜንሽን 44 ሚሊዮን ብር እንዲሰጥ ትእዛዝ ለወገጋን ባንክ የሰጡበት ደብዳቤ ቅጅ ኢሳት ደርሶታል።
ወ/ሮ አዜብ ትእዛዙን የሰጡት በ2007ዓም ሲሆን፣ ገንዘቡ የአጭር ጊዜ ብድር ሆኖ ዋስትናውን የትምእት ( ኢፈርት) ኩባንያ ይወስዳል ብለዋል።
ወ/ሮ አዜብ ባለቤታቸው ከሞቱ በሁዋላ የኢፈርት ስራ አስኪያጅነታቸውን ማስረከባቸው ቢነገረንም፣ አምና ሰኔ ወር ላይ በጻፉት ደብዳቤ ራሳቸውን የኢፈርት ስራ አስኪያጅ አድርገው አቅርበዋል።