ታኀሳስ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት ወጣቶችን በየአካባቢው እያፈሰ ከማሰሩም በላይ የተቃዋሚ መሪዎችን ሲያስፈራራ ከቆየ በሁዋላ መሪዎችን ይዞ ማሰር ጀምሯል።
በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ም/ል ሊ/መንበር አቶ በቀለ ገርባ እንዲሁም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ዋና ጸሃፊ የሆኑት የህግ ባለሙያውና ከ10 አመት በፊት በተደረገው ምርጫ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ደጀኔ ጣፋ ገለታ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው ታስረዋል።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በመንግስት ላይ በሚያደርሱት ጠንካራ ትችት ይታወቃሉ። በተመሳሳይ ዜና በጅማ ሂምና ዩኒቨርስቲ የሚማሩ 13 የኦሮሞ ተወላጆች ተማሪዎችን ለተቃውሞ ቀስቅሰዋል በሚል እየተፈለጉ ነው። የዩኒቨርስቲው የጥበቃና ደህንነት የስራ ሂደት ቢሮ ባወጣው ማስታወቂያ ገመችስ ታከለ፣ አሸናፊ ሌንጂሳ፣ አለማየሁ ገመቹ፣ መብራቱ ጅሬኛ፣ መሃመድ ሸምሲዲን፣ አብዲሳ በንቲ፣ ፋጂ ሙላት፣ አብደላ ተስሳ፣ ዘነበች ጌታቸው ፣በሻቱ ቃናአ፣ ቢራ ነጋሽ ደመቀ እንዲሁም አሰፋ ፋና ታህሳስ 14 በዩኒቨርስቲው ተገኝተው የዲሲፒሊን ኮሚቴው የሚሰጠውን ውሳኔ እንደከታተሉ ተጠርተዋል። በኦሮምያ በተካሄደው ህዝባዊ ተቃውሞ 85 ዜጎች በአጋዚ ወታደሮች ሲገደሉ ከ1 ሺ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ታስረዋል።