ታኀሳስ ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የንቅናቄው ከፍተኛ የአመራር አባል የሆነው እንደገለጸው የንቅናቄው ሰራዊት ዋልድባ አካባቢ የነበረውን ወታደራዊ ቀለበት በመስበር በአድርቃይ ላይ በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ጥቃት ፈጽሞ ከ29 በላይ ወታደሮችን ገድሏል። ጦርነቱ አሁንም ቀጥሎአል። በግንባር የተሰለፉ 6 አብሪዎች ወይም በቅኝት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ አባሎቻቸው ከፍተኛ ውጊያ አድርገው ጥይታቸው ማለቁን ተከትሎ በወያኔ እጅ ወድቀዋል ሲል ታጋይ ዘመነ አክሎ ገልጿል። ከተከዜ ወደ መሃል አገር እየገሰገስን መሆኑን መንግስት ራሱ የለቀቀው መረጃ ያመለክታል የሚለው ታጋይ ዘመነ፣ መተማ አካባቢ በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች አሁንም ድረስ ትግል በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጿል።
ታጋይ ዘመነ መተማ ዘባጭ ውሃ አካባቢ ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ ከ9 እስከ 10 ሰአት በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ባደረሱት ጥቃት 19 የልዩ ሃይል አባላት መገደላቸውንና 20 ቁስለኞች ሸዲ ሆስፒታል ገብተው በመታከም ላይ መሆናቸውም ገልጿል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩትን ህዝባዊ ተቃውሞች የአርበኞች ግንቦት7 ንቅናቄ ሙሉ ድጋፉን እየሰጠ መሆኑን ታጋይ ዘመነ አክሎ ገልጿል ፡፡ መንግስት 5 የአርበኞች ግንቦት7 አባላትን አድርቃይ ላይ መማረኩን መግለጹና ጦርነት መካሄዱን ማመኑ ይታወቃል።